የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ10ኛ ሳምንት ዛሬ በሚከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

0
431

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ቡና ከሻሼመኔ፣ሲዳማቡና ከ አዳማ ከተማ ዛሬ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ በ10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ቀን 9ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከሻሸመኔ ከተማ ይጫወታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ላይ ተቀምጧል። አሠልጣኝ ነፃነት ክብሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ በገጠሙበት ጨዋታ ላይ በአመዛኙ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ነበር የመረጡት፡፡ በጨዋታውም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ችለዋል፡፡ ይህን የአጨዋወት ስልት ዛሬም ሊከተሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

በዛሬው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ ባለፈው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት ይህ ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል፡፡ ሻሸመኔ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ተጫውቶ በሦስት ነጥብ እና በሰባት የግብ ዕዳ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

አሠልጣኝ ዘማርያም ቡድኑን ከተረከቡ በኃላ በመከላከሉ ረገድ እምርታን እያሳየ ይገኛል። ሻሸመኔዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎችም ሁለት ነጥብ ማስመዝገባቸው ለመነቃቃታቸው አይነተኛ ማሳያ ኾኗል።

በተለይ ቡድኑ ከባሕር ዳር ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ የነበራቸው የመከላከል ጥንካሬ በጣም የተሻሻለ ነበር፡፡ ነገርግን አሁንም በማጥቃቱ ረገድ ግቦችን ለማስቆጠርም ኾነ እድሎችን ከመፍጠር አንፃር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ አማካዩ ማይክል ኔልሰን በቅጣት እንዲሁም ቻላቸው በጉዳት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ጨዋታውን ሚካኤል ጣዕመ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል፡፡ አሸብር ታፈሰ እና ኤፍሬም ኃይለማሪያም በረዳትነት ዳኝነት ተመድበዋል፡፡ ኢንርናሽናል ረዳት ዳኛ ኤፍሬም የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ናቸው።

ምሽት 12ሰዓት ከጨዋታ ጨዋታ መነቃቃት ላይ የሚገኘውን ሲዳማ ቡና ከሰሞኑ የውጤት ቀውስ ውስጥ ከሚገኘው አዳማ ከተማ ጋር የሚጨወት ይኾናል። ሲዳማ ቡና በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታ አድርጎ በአስራ አንድ ነጥብ እና በአንድ ንጹህ ግብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ቡድኑ ኢትዮጵያ መድኅንን በይገዙ ቦጋለ ግብ አማካኝነት ረትተዋል፡፡ ተጫዋቹ በ2014 የውድድር ዘመን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ይገዙ ዘንድሮ በአምናው አቋሙ አይገኝም፡፡ ተጫዋቹ ወደ ግብ ማስቆጠር መመለሱም ለቡድኑ መልካም ነገር ነው፡፡

በተጫዋች ረገድ ሲዳማ ቡና መሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ መኾኑ ታውቋል። የሲዳማ ቡና ተጋጣሚ አዳማ ከተማ በዘጠኝ ጨዋታ አስራ ሦስት ነጥብ እንዲሁም አንድ ንጹህ ግብ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ 8ኛ ላይ ይገኛል። አዳማ ከተማ ከሰሞኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በማጥቃቱ ረገድ ተዳክሞ ታይቷል።

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ መርሐ ግብሮች ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩ ለመዳከሙ አብነት ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ውጤት ይዘው ለመውጣት ያለባቸውን የማጥቃት ድክመት አርመው መቅረብ የግድ ይላቸዋል።

ቡድኑ ቻርልስ ሪባኑ ለእረፍት ወደ ሀገሩ አቅንቶ እስካሁን ባለመመለሱ ከዛሬው የጨዋታ ስብስብ ውጭ ኾኗል፡፡ አድናን ረሻድ ደግሞ በጉዳት ከጨዋታ ውጭ መኾኑ ተረጋግጧል።
ይህን ጨዋታ ባህሩ ተካ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል፡፡ ለዓለም ዋሲሁን እና ወጋየሁ አየለ ረዳት ዳኞች ናቸው፡፡ ዳንኤል ይታገሱ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመኾን ጨዋታውን ይመራሉ።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here