የባለታሪኮቹ ፍጥጫ!

0
328

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በአውሮፓ ዋንጫው እንደ ሁለቱ ሀገራት ብዙ ዋንጫዎችን ከፍ ያደረገ የለም፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከፊት በመቅደም ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትን ያስከትላሉ፡፡ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስም ያላቸው ናቸው፡፡ ታላላቅ ተጨዋቾችን በማውጣትም ለዓለም እግር ኳስ አበርክተዋል፤ ጀርመን እና ስፔን፡፡
የ2024 የጀርመን የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ፡፡ ለዋንጫ የተጠበቁ አራት ታላላቅ ሀገራት እርስ በእርሳቸው የሚገናኙባቸው የዛሬዎቹ ጨዋታዎች በጉጉት እየተጠበቁ ነው፡፡ አዘጋጇ ጀርመንን ከስፔን፣ ፖርቹጋልን ከፈረንሳይ ያገናኘው ጨዋታ እስኪጀምር ድረስ የቸኮሉ የእግር ኳስ አፍቃሪያን በዝተዋል፡፡

በደገሰችው ድግስ በጥሩ ብቃት ላይ የምትገኘው ጀርመን ዋንጫውን አሳልፋ ላለመስጠት የዛሬውን ከባድ ጨዋታ በድል መወጣት ይጠበቅባታል፡፡ በውድድሩ ያደረጋቸቸውን አራት ጨዋታዎች ሁሉንም በድል የተወጣችው ስፔንም የዋዛ ተጋጣሚ አይደለችም፡፡ በወጣት ተጨዋቾች የፊት መስመሯን የምትመራው ስፔን በውድድሩ መቶ በመቶ የማሸነፍ ክብረ ወሰኗን ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡

ምሽት 1፡00 በስቱት ጋርት ሜርሲዲ ቤንዝ አሬና የሚደረገው የጀርመን እና የስፔን ጨዋታ የታላላቆቹ ፍልሚያ ኾኗል፡፡ ቢቢሲ በዘገበው የአውሮፓ ዋንጫ ከሁለቱ ምርጥ ቡድኖች አንደኛውን ይለያል ብሏል፡፡ በስቱትጋርት የሚደረገው ጨዋታ ምርጡ ጨዋታ ሊኾን እንደሚችልም ተገምቷል፡፡ ስለ ምን ቢሉ በዓለም ፊት ከምርጥም ምርጥ ኾኖ ለመውጣት የሚደረግ ፍሊሚያ ነውና፡፡

ጀርመናውያን በብሔራዊ ቡድናቸው ያላቸው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ከውድድሩ በፊት ታላቅ ግምት ያልተሰጠው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሁን ላይ ግን በእያንዳንዱ ጨዋታ አሸናፊነቱ እየጨመረ ነው ይላል ቢቢሲ፡፡ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ስምንት ውስጥ ካሉ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የተሟለው ቡድን ይመስላል ነው የተባለው፡፡

የጀርመኑ አምበል ኢልካይ ጉንዶጋን ብሔራዊ ቡድናቸው ምርጥ ቡድን መኾኑን ተናግሯል፡፡ የቀድሞውን የባየርን ሙኒክ አሠልጣኝ ሃኒስ ፍሊክን አሰናብታ ሌላኛውን የቀድሞ የባየርን ሙኒክ አሠልጣኝ ጁሊያን ኔግሊስማን የሾመችው ጀርመን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለች፣ ውጤቷ እያማረ ሄዷል፡፡ ጀርመን እያሳየቸው ባለው ድንቅ አቋም አሁን በመላ ሀገሪቱ የተጠናከረ የአንድነት ድጋፍ አለ እየተባለ ነው፡፡

አሠልጣኝ ጁሊያን ኔግሊስማን አማካዩ ቶኒ ክሩስን ወደ ብሔራዊ ቡድን ድጋሜ እንዲመለስ ማድረጋቸው እና ወጣቱ ተጨዋች ጀማል ሙሲያላን የተጠቀሙበት መንገድ ትልቁ ችሎታቸው እንደኾነ እየተነገረ ነው፡፡ አስቀድሞ ከውድድሩ በኋላ ራሱን ከእግር ኳስ እንደሚያገል ያሳወቀው ክሩስ አሁን ላይ በቡድናችን የተለየ እምነት አለን፤ ጨዋታዎችን እያሸነፍን ነው ብሏል፡፡ ብዙ መሄድ እንፈልጋለን ያለው ክሩስ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ያለው ስሜት ያን ማድረግ የሚያስችል መኾኑንም ተናግሯል፡፡

ጀርመን እና ስፔን ከተገናኙባቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ በአቻ ውጤት ነው የተለያዩት፡፡ በሦስቱም ጨዋታዎች በአንድ አቻ ጨዋታው ተጠናቅቋል፡፡ አንደኛው ጨዋታ ግን ስፔንን ባለ ድል አድርጓል፡፡ በ2020 በተደረገው ጨዋታ ስፔን ጀርመንን 6 ለ 0 አሸንፋታለች፡፡ አሁን ላይ በስፔን ብሔራዊ ቡድን ሥብሥብ ውስጥ የሚገኘው ፌራን ቶሬስ ደግሞ በዚህ ጨዋታ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሦስታ (ሀትሪክ) ሰርቶ ነበር፡፡ ይህ ድል ስፔንን በሥነ ልቦና የበላይ እንድትኾን ያደርጋታል ይላሉ ተንታኞች፡፡

እንግሊዛዊው የተከላካይ መስመር ተጨዋች የነበረው ማቲው አፕሰን ከቢቢሲ ራዲዮ ጋር ባደረገው ቆይታ “የስፔን ብሔራዊ ቡድን በጣም የተሟላው ቡድን ነው” ብሏል፡፡ ማቲው ኳሱን ከእነርሱ እግር ማውጣት ካልተቻለ እጅግ አደገኛ ቡድን እንደኾነም ነው የሚገልጸው፡፡ የስፔን ብሔራዊ ቡድን የፊት መሥመር ተጫዋቾች ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ድንቅ ብቃታቸውን እያሳዩ ነውም ብሏል፡፡

ቢሶከር በዘገባው ከ2014 የዓለም ዋንጫ ድል በኋላ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በታላላቅ ውድድሮች ላይ ደካማ አቋም ሲያሳይ ቆይቷል ብሏል፡፡ አሁን ላይ ግን ያሸበረቀ ቡድን እየኾነ መጥቷል ነው ያለው፡፡ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከዘጠኝ ወራት በፊት ከነበረው አቋም እጅግ የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ዘግቧል፡፡

በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ሦስት ሦስት ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙት ጀርመን እና ስፔን ዛሬ የሚያሸንፈው ቡድን ምን አልባትም ለዋንጫ ሊደርስ ይችላል የሚሉ ግምቶች በርክተዋል፡፡ በእርግጥ ሌሎች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖችም ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡

ቶኒ ክሩስ ላለፉት አሥርት ዓመታት የኖረባትን ስፔንን በተቃራኒ ይገጥማል፡፡ ክሩስ ስፔናዊ ተጨዋቾችን ማወቅ ለጨዋታው ብዙ ጥቅም እንደሌለውም አመላክቷል፡፡ ሁሉም ተጨዋቾች የታወቁ ናቸው፤ የተለየ ነገር መጠበቅ አይገባም ነው ያለው፡፡ ከሁለቱ ታላላቅ እና ባለታሪክ ሀገራት የትኛው ይሰናበታል? የትኛውስ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፋል? ለሚሉት ጥያቄዎች የምሽቱ የስቱትጋርቱ ጨዋታ ምላሽ ይኖረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here