የማያረጅ ጉልበት!

0
201

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብራዚላዊቷ እግር ኳሰኛ ማርታ ቪዬራ ዳ ሲልቫ አሁን እድሜዋ 38 ደርሷል። ያም ኾኖ ግን ፈረንሳይ በምታዘጋጀው ኦሎምፒክ ላይ በእግር ኳስ የብራዚል ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ወክላ ለስድስተኛ ጊዜ ትጫወታለች፡፡ ማርታ ለብራዚል በስድስት የዓለም ዋንጫዎች ላይም ተሰልፋለች፡፡በ118 ግቦች የብራዚል ሴቶች ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰን ባለቤትም ናት፡፡

ማርታ በ23 ጨዋታዎች 17 ግቦችን በማስቆጠር በሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ታሪክ የምንጊዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ናት፡፡ ይሄው ክብረ ወሰን በወንዶቹ የዓለም ዋንጫም ላይ ያልታየ ነው፡፡ በአምስት የዓለም ዋንጫዎች ላይ ግብ በማስቆጠርም በሴቶችም ኾነ በወንዶች ያልተመዘገበ ክብረ ወሰን ባለቤትም ናት፡፡ ስድስት ጊዜ ጊዜ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ተብላም ተመርጣለች፡፡

ማርታ በ2004 አቴንስ እና በ2008 ቤጂንግ (እ.ኤ.አ) የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ሀገሯን ወክላ የብር ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡ በሁለቱም ውድድሮች ላይ ከብራዚል የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያውን የነጠቀችው ደግሞ አሜሪካ ናት፡፡ የ38 ዓመቷ ማርታ የዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን የምታደርገው የመጨረሻ ጨዋታዋ እንደኾነ አሳውቃለች፡፡

የብራዚል ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኙ አርቱር ኤሊያስ “ማርታ የዓለማችን ምርጧ ተጫዋች ናት፤ ለሌሎች ሴቶችም በብዙ ታስተምራለች፤ ለብራዚል የሴቶች እግር ኳስ ኦሎምፒክ ቡድንም በተገቢው መልኩ ትመጥናለች፤ የኔ ፍላጎት ቡድናችንን እንድታግዘው ብቻ ነው፤ የእሷ ፍላጎት ደግሞ በሁሉም ውድድሮች ላይ ማሸነፍ ነው” ብለዋል፡፡ ማርታ አሁን ላይ ለብራዚሉ ኦርላንዶ ፕራይድ ክለብ በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡

በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ስመ ገናናዋ ማርታ በ38 ዓመቷ ለብራዚል ኦሎምፒክ ቡድን ከተጫወተች በኋላ ራሷን ከብሔራዊ ቡድኑ ብታገልም ከብራዚላዊያን ልብ ውስጥ ምንጊዜም የማትገለል ተጫዋች ናት፡፡ በርካታ የእግር ኳስ ተጨዋቾች በ30ዎቹ እድሜያቸው ላይ ከእግር ኳሱ በሚገለሉበት ወቅት እስከ 38 ዓመቷ በጥሩ አቋም የዘለቀችው ማርታ የማያረጅ ጉልበትን የታደለች ስለ መኾኗ በእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ እያስመሰከረች ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here