ሕልም እና እውነት በአንድ ሜዳ!

0
262

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እግር ኳስ የደስታ ማዕድ አቅርባለች፡፡ ሕልም እና እውነት በአንድ ሜዳ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ሕልም እና እውነት የሚገናኙበትን ቀን በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡ የጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ሕልመኛውን እና እውነተኛውን አገናኝቷል፡፡ የአውሮፓ ሀገራት እየተፋለሙበት በሚገኘው ውድድር ታላላቆቹ ሀገራት በሩብ ፍጻሜው ተገናኝተዋል፡፡

አዘጋጇን ሀገር ጀርመን በድንቅ ብቃት ላይ ከምትገኘው ስፔን ጋር አገናኝቷል፡፡ የክርስቲያኖ ሮናልዶዋ ሀገር ፖርቹጋል ደግሞ ከኪሊያን ሜባፔዋ ሀገር ፈረንሳይ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ የዓለም ከዋክብቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ኪሊያን ሜባፔ የሀገራቸውን ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት እየመሩ ይፋለማሉ፡፡

ሜባፔ በዘመኑ እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ መኾንን ሲመኝ ኖሯል፡፡ ፖርቹጋል ማዴራ በድህነት ከተሸነቆረች ጎጆ የወጣው ሮናልዶ በጠንካራ ሠሪነቱ ባስመዘገበው እጥፍ ድርብ ስኬት ዓለምን እያስደነቀ ለዓመታት ዘልቋል፡፡ በአያሌ እግር ኳስ ሜዳዎች እንደ አንበሳ ሲያገሳ ታይቷል፡፡

በእርሱ ወገን የተሰለፉትን ሲያስቦርቅ፣ በተቃራኒው የሚገኙትን ደግሞ አንገት ሲያስደፋ ኖሯል፡፡ እርሱ ከድል ላይ ድል እየጨመረ ሁልጊዜም ድል የሚርበው፣ ስኬት የማያኮራው፣ ዕውቅና እና ገንዘብ ከሥራው የማያዘናጋው፣ ሁልጊዜም ለአዲስ ስኬት እና ድል የሚተጋ የእግር ኳስ ጀግና ነው፡፡

ከዓመታት በፊት በልቶ ለማደር ይቸገር የነበረው ሮናልዶ ከዓመታት በኋላ ከስኬት ላይ ስኬት ደራርቧል፡፡ በሃብት እና በዝናም ናኝቷል፡፡ ዓለም ላይ እንደ እርሱ የሚወደድ ተጨዋች የለም ይላሉ የስፖርት ተንታኞች፡፡ ለዚህ ደግሞ ሮናልዶን አርዓያ አድርገው ያደጉ ተጨዋቾችን፣ ሮናልዶን በፌስቡክ፣ በኢንስታግራም እና በሌሎች የማኅበራዊ መገኛ አውታሮች የሚከተሉትን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለም አድናቂዎችን፣ እግሩ በተንቀሳቀሰባቸው ሀገራት ሁሉ እርሱን ለማየት እና ከእርሱ ጋር ፎቶ ለመነሳት የሚተራመሱትን በማሳያነት ያነሳሉ፡፡

በዓለም ላይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደ ሮናልዶ ብዙ ተከታይ ያለው ሰው የለም፡፡ በበርካቶች በመወደድ እና በርካቶች እንዲከተሉት በማድረግ ቀዳሚው ተጨዋች ነው፡፡ ይህ በስፖርት ብቻ አይደለም በየትኛውም ዘርፍ ከእርሱ ጋር የሚስተካከል ተከታይ ያለው ሰው የለም፡፡ ለዚህ ያበቃው ደግሞ ለሙያው በከፈለው መስዋዕትነት እና ባስመዘገበው ስኬት ነው፡፡

በታላላቆቹ የአውሮፓ ሊጎች በእንግሊዝ፣ በስፔን እና በጣሊያን እንዳሻው ቦርቋል፡፡ በደረሰባቸው ሀገራት ሁሉ ኮኮብ በመኾን የወርቅ ጫማዎችን ወስዷል፡፡ ዋንጫዋችንም ደጋግሞ አንስቷል፡፡ የአውሮፓውን የስኬት በር ዘግቶ ወደ ኢሲያ ሳውዲ አረቢያ ሄዶም የዓለም ዐይኖች ሁሉ እንዲከተሉት አድርጓል፡፡
ከዋክብትም እርሱ ከደረሰባት ሀገር ሳውዲ አረቢያ ለመድረስ ጎርፈዋል፡፡ በእግር ኳስ የጠንካራ ሠራተኛነት እና የስኬት ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰደው ሮናልዶ አሁን ላይ እየመጡ ላሉ ከዋክብት አርዓያቸው ነው፡፡

እርሱን አርዓያ አድርገው ካደጉ እና በእግር ኳስ እየደመቁ ከሚገኙ ከዋክብት መካከል ደግሞ ኪሊያን ሜባፔ አንደኛው ነው፡፡ ኪሊያን ሜባፔ በለጋ እድሜው በሮናልዶ ምስሎች በተለጣጠፈች ማደሪያ ቤቱ ተቀምጦ አንድ ቀን እንደርሱ መኾንን ሲያልም ኖሯል፡፡ ያ ትናንት ሕልመኛ የነበረው ታዳጊ ዛሬ ላይ ቀድመው ከሚጠሩ ከዋክብት መካከል አንደኛው ኾኗል፡፡ በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ሀገሩን በአምበልነት እየመራ ወደ ጀርመን ያቀናው ሜባፔ ከአርዓያው እና ከሕልሙ ሰው ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ሊፋለም ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

በሩብ ፍጻሜው ፈረንሳይ እና ፖርቹጋል መገናኘታቸውን ተከትሎ የሮናልዶ እና የሜባፔ ፍጥጫ ተጠባቂ ኾኗል፡፡ ሕልም እና እውነት በአንድ ሜዳ ላይ ተገናኙ እየተባለ ነው፡፡ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዬ ሮማኖ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ኪሊያን ሜባፔ አርብ ፊት ለፊት ይገናኛሉ፤ ሕልም ወደ እውነታ ሲሄድ ብሎ ጽፏል፡፡

በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ፖርቹጋል እና ፈረንሳይ በፍጻሜው ሲጫወቱ ሜባፔ የሕልሙን ሰው ከሀገሩ በተቃራኒ ሲጫወት በቤት ቁጭ ብሎ ይመለከት ነበር፡፡ በአንድ በኩል እትብቱ የተቀበረባት ሀገሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሲወደው የኖረው ሮናልዶ በተቃራኒ ተገናኝተው፡፡

ከስምንት ዓመታት በኋላ በአውሮፓ ዋንጫ ውድድር በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይ እና ፖርቹጋል ተገናኝተዋል፡፡ ከዓመታት በፊት ከሀገሩ በተቃራኒ ኾኖ ሲጫወት ያየውን የሕልሙን ሰው ከስምንት ዓመታት በኋላ ራሱ የሀገሩን መለያ አጥልቆ፣ ለዛውም ሀገሩን በአምበልነት እየመራ ከሕልሙ ሰው ጋር በተቃራኒ ይጫወታል፡፡

በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ኢደር ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ፖርቹጋል ዋንጫውን እንድታነሳ አድርጓል፡፡ ከዓመታት በኋላ በሩብ ፍጻሜው ለመጫወት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡ ፈረንሳይ ዋንጫ ያሳጣቻትን ሀገር ፖርቹጋልን ትበቀላለች ወይስ ፖርቹጋል ሌላ ድል ታስመዘግባለች የሚለው እንቆቅልሽ ይፈታ ዘንድ ቀናት ቀርተዋል፡፡

ቢቢሲ በዘገባው የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢው እና ባለታሪኩ ተጨዋች ሮናልዶ አሁንም ቡድኑን እየመራ ጀርመን ላይ ነው፤ ዐይኖች ሁሉ በእርሱ ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይላል ቢቢሲ በ2024 የጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ያደረገው ሮናልዶ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ በውድድሩ እንደ እርሱም በርካታ ኳሶችን መሞከር የቻለ ተጨዋች የለም፡፡ ያም ኾኖ ሮናልዶ ትኩረት የሚስብ ተጨዋች ነው፡፡

የፈረንሳይ እና የፖርቹጋል ጨዋታ የፊታችን አርብ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም በጀርመን ሐምቡርግ ይደረጋል፡፡ የታላላቆቹ ሀገራት እና የታላላቆቹ ከዋክብት ፍጥጫ ከወዲሁ ትኩረት ስቧል፡፡ ፈረንሳይ ወይስ ፖርቹጋል? ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወይስ ኪሊያን ሜባፔ? የአርብ ምሽቱ የሐምቡርጉ ጨዋታ ምላሽ ይኖረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here