አፍሪካውያንን በአውሮፓ ዋንጫ!

0
204

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጀርመን አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው 17ኛው የአውሮፓ ሀገራት ዋንጫ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድ እና ስፔንን ወደ ሩብ ፍጻሜው ይዟቸው ተጉዟል፡፡ በ 24/10/2016 ዓ.ም ቤልጅየም ከፈረንሳይ እና ፖርቱጋል ከስሎቬንያ እንዲሁም በ25/10/2016 ዓ.ም ሮማንያ ከኔዘርላንድ እና ኦስትሪያ ከተርኪዬ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ቀሪ አራቱ ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚቀላቀሉትን ሀገራት ያሳውቀናል፡፡

በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዝ ተጨዋቾች የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎቹ ድምቀት ኾነው ቀጥለዋል፡፡ እነዚህን ከስካይ ስፖርት ያገኘናቸውን ተጨዋቾች ለአብነት ያህል ጠቀስን እንጂ በርካታ አፍሪካውያን ተጫዋቾች በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን አልዘነጋነውም፡፡

ትውልደ ካሜሮናዊው ብሪል ኢምቦሎ አሁን ላይ የስዊዘርላንድን የፊት መስመር እየመራው ይገኛል፡፡ የኔዘርላንድ የፊት መስመር ተሰላፊው ሜምፊስ ዴፓይም የዘር ሀረጉ ጋና ነው፡፡ የፈረንሳይ የመሐል ሞተሩ ኒጎሎ ካንቴም የዘር ሀረጉ የሚመዘዘው ከማሊ ነው፡፡ የዴሞክራቲክ ኮንጎው ሮሜሉ ሉካኩ ለቤልጅየም፣ ትውልደ ሴኔጋላዊው ሊሮ ሳኔ ለጀርመን እና የዘር ሀረጉ ከካሜሮን የሚመዘዘው ኪሊያን ምባፔም ለፈረንሳይ በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

የቶጎ ተወላጁ ኮዲ ጋክፖ ለኔዘርላንድስ፣ የሴራሊዮኑ አንቶኒ ሩዲገር ለጀርመን፣ ካሜሮናዊው ኦሬሊየን ሾሚኒ ለፈረንሳይ፣ የናይጄሪያዎቹ ጀማል ሙሲያላ እና ቡካዮ ሳካ ደግሞ ለጀርመን እና ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድኖች በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ናይጀሪያዊ ጆናታን ታህም የጀርመንን የተከላካይ ክፍል አለኝታ ነው። ስፔን በወጣቶቹ ኒኮ ዊሊያምስ እና ላሚን ያማል በአውሮፓ ዋንጫው በከፍታ ላይ ትገኛለች። ዊሊያምስ ከጋና ያማል ደግሞ ከሞሮኮ ይመዘዛል የዘር ግንዳቸው።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ተወላጆቹ ስቲቭ ማንዳንዳ እና ኤድዋርዶ ካማቪንጋ ለፈረንሳይ የሚጫወቱ አፍሪካውያን ኮከቦች ናቸው፡፡ በተለይ ፈረንሳይ በርካታ አፍሪካዊ የዘር ሀረግ ያላቸውን ተጫዋቾች በቡድኗ ውስጥ አሠባሥባ የአውሮፓ ዋንጫን ለማሳካት እየጣረች ነው፡፡

የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዘው ከዋክብት በአውሮፓ ዋንጫው ላይ ለሚያሳዩት ድንቅ ክህሎት አወዳሾቻቸው የሚበዙትን ያህል ስህተቶቻቸውን ከቆዳ ቀለም ጋር በማገናኘት የሚወቅሷቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህ አብነት የሚኾነው ደግሞ በ2020 እ.ኤ.አ እንግሊዝ በአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ከጣሊያን ጋር በመለያ ምት ስትለያይ የመለያ ምቱን ያባከኑት እነ ቡካዮ ሳካ ላይ የደረሰባቸውን የዘረኝነት ወቀሳ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here