ባሕር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ይጫወታሉ።

0
226

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርቡ ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርተው በመውጣት ለሳምንታት የቆዩበትን ደረጃ ለኢትዮጵያ ቡና አሳልፈው የሰጡት ባሕር ዳር ከተማዎች ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ነው አዳማ ከተማን የሚገጥሙት። የጣና ሞገድ በቀላሉ መረቡን የማያስደፍር የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን ነው። ላለፉት 13 ጨዋታዎችም ሽንፈት ያልገጠመው በተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ ነው።

ቡድኑ በ13 ጨዋታዎች ያለሽንፈት ከመጓዙ በተጨማሪ በዘጠኝ ጨዋታዎች መረቡን ሳያደፍር መውጣቱ ጥሩ የመከላከል አቋም ላይ መገኘቱን ያሳያል። ይሁን እና ለጣና ሞገድ ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች በጉዞው ላይ እክል ኾኖበታል። ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉን መሪ ነጥብ ያስጣለው የአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ሥብሥብ ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ካገኘ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመገናኘት ይጠቅመዋል። ከዚህ በተጨማሪ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የመጨረስ ዕድላቸውን ለመጠቀም ድሉ አስፈላጊያቸው ነው። በባሕር ዳር ከተማ በኩል ሙሉ ሥብሥቡ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር መረጃ አዳማ ከተማ ነጥቡ አርባ አራት ደረጃው ደግሞ አምስተኛ ነው። የአዳማ ከተማ ሰሞነኛ ብቃት ጥሩ የሚባል ነው። በመኾኑም ደረጃቸውን ለማሻሻል በሁለት ነጥብ ከፍ ብሎ ከተቀመጠው ባሕር ዳር ከተማ ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በጨዋታው አዳማ ከተማ የቻርለስ ሪባኑን ግልጋሎት አያገኙም። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተው ባሕር ዳር ከተማ ስድስት በማሸነፍ የበላይ ነው። አዳማ ሁለት ጊዜ አሸንፏል። አንዱን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here