አንቱታ የሚገባቸው አሠልጣኝ!

0
198

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በእግር ኳስ በተጫዋችነት እና አሠልጣኝነት ውጤታማ መኾን ብዙዎች የሚታደሉት አይደለም። ጥሩ ተጫዋች የነበሩ በአሠልጣኝነት ሲሰለፋ ግን ያልተሳካላቸው ብዙዎች ናቸው። ዲያጎ ማራዶና፣ ዋይኒ ሩኒ እና ቴሪ ኦነሪን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በአንጻሩ ኳስን በትልቅነት ያልተጫወቱ ግን በአሠልጣኝነት ዓለምን ያስደመሙም በጆዜ ሞሪንሆ ምሳሌነት ይወከላሉ።

በተጫዋችነትም በአሠልጣኝነትም በስኬት ከሚጠቀሱት ውስጥ ደግሞ ዲዴር ዴሾ አንዱ ናቸው። ዴሾ አሁን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ናቸው። በተጫዋችነት ዘመናቸው በማርሴይ፣ ቼልሲ እና ጁቬንቱስ ተጫውተዋል። ሁለት የፈረንሳይ ሊግ 1 እና ሦስት የጣሊያን ሴሪኤ ዋንጫ ክብር ባለቤትም ናቸው። የተጫዋቾች ሁሉ ህልም በኾነው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም ሁለት ጊዜ ነግሰዋል።

በተጫዋችነት ዘመናቸው በወቅቱ ከነበሩ ምርጥ የተከላካይ አማካዮች ውስጥ አንዱ ነበሩ ይላቸዋል ቢቢሲ። በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የነበራቸው ሚናም የሚደነቅ ነው። ፈረንሳይ የ1998ቱን የአለም ዋንጫ ስታነሳ የቡድኑ አምበል ዴሾ ነበር። በወቅቱ የቡድን አጋሩ የነበረው ሊሊያን ቱራም “ዴሾ ምርጥ እና የእውነተኛ መሪነው ድሉ እንዲገኝም ትልቁ ሥራ የእሱ ነው “ሲል መመስከሩን ቢቢሲ ስፖርት አስታውሷል።

የተጫዋችነት ዘመናቸው እንዲህ የሚቀናበት ዲዴር ዴሾ ራሳቸውን ከተጫዋችነት ካገለሉ በኋላ ወደ አሠልጣኝነት ሥራ ገብተዋል። በሞናኮ፣ ማርሴይ እና ቼልሲ ከሠሩ በኋላ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ከያዙ አሁን 12 ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታት ፈረንሳይን ሦስት ጊዜ በዓለም ዋንጫ ይዘው ቀርበዋል። አንድ ጊዜ ዋንጫ ሲያነሱ፣ በቅርቡ በአርጀንቲና ተሸንፈው ዋንጫ ያጡበት ሌላኛው ነው። ቀሪው ደግሞ በ2014ቱ የብራዚል ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ድረስ የተጓዙበት ነው።

በአውሮፓ ዋንጫም በተለይ በ2016 ለዋንጫ ደርሰው በፖርቱጋል የተሸነፍበት ውጤት ይጠቀሳል። የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በየጊዜው ኮከቦች የሚፈሩበት ነው። ኮከቦችን ለአንድ ዓላማ በማዘጋጀት ለፈረንሳይ ውጤት ማስገኘት ደግሞ ከአሠልጣኝ ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ ዲዴር ዴሾ ሁነኛ ሰው ኾነው ተገኝተዋል።

የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ የአሠልጣኝ እና ተጫዋቾች ግልጽ አለመግባባት ታይቶበት ብዙ ትችቶችን አስተናግዶ ነበር። ውዝግቡን ተከትሎ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑን ለቀው መውጣታቸውም ይታወሳል። የወቅቱ ቡድን በዓለም ዋንጫው ከምድብ እንኳ ማለፍ ባለመቻሉ በብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ዴሾ እንዲህ በሥነ ምግባር ጥላሸት የተቀባውን ቡድን ወደ አንድነት እና ስኬት መልሰውታል። ሰውየው በጠንካራ የግለሰብ አያያዝ እና ጥብቅ መርሕ የሚያምኑ መኾናቸው ደግሞ ለስኬታቸው ምክንያት ነው። ፈረንሳዉያን በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ዋንጫውን ስለማንሳት እያሰቡ ነው። ለዚህም ከኮከባቸው ኪሊያን ምባፔ በተጨማሪ በብልሁ አሠልጣኛቸው ትልቅ እምነት ጥለዋል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here