የአሸናፊነት ቅድሚያ ግምት የተሰጣት ፈረንሳይ ከኦስትሪያ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

0
249

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ 4 የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ፈረንሳይ ከኦስትሪያ ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታደርጋለች። 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ 4ኛ ቀኑን የያዘ ሲኾን ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በምድብ 4 ፈረንሳይ ከኦስትሪያ ጋር ከምሽቱ 4 ሰዓት 54 ሺህ 600 ተመልካች በሚያስተናግደው ዱሲልዶርፍ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሁለቱ ሀገራት በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 በተካሄደው የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ውድድር ፈረንሳይ በኪሊያን ምባፔ እና ኦሊቨር ጂሩድ ግቦች 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው። ኦስትሪያ እና ፈረንሳይ እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 25 ጊዜ ተገናኝተው ፈረንሳይ 13 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። 9 ጊዜ ያሸነፈችው ደደግሞ ኦስትሪያ ናት። ሦስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

ሀገራቱ ባለፉት 5 ጨዋታዎች በነበራቸው የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ፈረንሳይ 3 ጊዜ ስታሸንፍ ኦስትሪያ 1 ጊዜ አሸንፋለች። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ኦስትሪያ በአውሮፓ ዋንጫ ለ4ኛ ጊዜ እየተሳተፈች ነው። የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ፈረንሳይ ደግሞ በአሕጉራዊው መድረክ 11ኛ ተሳትፎዋ ኾኖ ተመዝግቧል።

ሁለቱ ሀገራት ለ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ያለፉት አስደናቂ በሚባል የማጣሪያ ጨዋታ ግስጋሴ ነው። ኦስትሪያ በነበረችበት ምድብ 6 በ19 ነጥብ ቤልጂየምን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን በምድብ 2 ፈረንሳይ 2 ነጥብ ብቻ በመጣል በ22 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቃለች።

የ65 ዓመቱ ጀርመናዊው የኦስትሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ራልፍ ራኚክ ቡድኑ በጥሩ ብቃት ላይ ይገኛል፤ በዛሬው ጨዋታ ፈረንሳይን ማሸነፍ የሚያስችል አቅም አለን ብሏል። ጀርመናዊ አሰልጣኝ ኦስትሪያን በ2022 ከተረከቡ በኋላ ቡድኑ ውጤታማ በማድረግ ላከናወኑት ስራ አድናቆት እየተቸራቸው ነው።

የ55 ዓመቱ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሾ ከኦስትሪያ ጋር የምናደርገው ጨዋታ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም ወሳኝ ጨዋታ ነው ሊባል አይችልም፤ የመጀመሪያ ጨዋታን ማሸነፍ በውድድሩ ላይ ለሚኖረን ጉዞ ወሳኝ ነው ሲል ገልጿል። በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኦስትሪያ 25ኛ፤ ፈረንሳይ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የ40 ዓመቱ ስፔናዊ ጂሰስ ጂል ማንዛኖ የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ። በምድብ 4 ትናንት በተደረገ የመጀመሪያ ጨዋታ ኔዘርላንድ ፖላንድን 2 ለ 1 አሸንፋለች። በምድብ 5 ሮማኒያ ከዩክሬን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ይጫወታሉ። ሮማኒያ በአውሮፓ ዋንጫ 6ኛ ተሳትፎዋን የምታደርግ ሲሆን ተጋጣሚዋ ዩክሬን በአህጉራዊው መድረክ ስትሳተፍ የዘንድሮው ለ4ኛ ጊዜ ነው።

በምድብ 5 ቤልጂየም ከስሎቫኪያ ከምሽቱ 1 ሰዓት በፍራንክፈርት አሬና ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ቤልጂየም በአውሮፓ ዋንጫው ለ7ኛ ጊዜ እንዲሁም ስሎቫኪያ ራሷን የቻለች ሀገር ከመሆኗ ወዲህ በውድድሩ ላይ ስትሳተፍ የአሁኑ ለ3ኛ ጊዜ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here