ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መቻል ይበልጥ ወደ ዋንጫው የሚጠጋበትን ነጥብ ለማግኘት ከፋሲል ከነማ ጋር በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ቀን 9 ሰዓት ላይ ይጫዎታል። በ40 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ግቡን ያላስደፈረ እና ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን ነው። ይህ ጠንካራ ጎኑ በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ቡድኖች ተርታ ያስመድበዋል።
አፄዎቹ በእርጋታ ኳስን መስርተው ለመጫዎት የሚጥርሩ እንደኾነ አያጠያይቅም። ታዲያ የቡድኑን የፊት መስመር ለማጠናከር የመሀል ሜዳ ተጫዋቾቻቸውን ወደ ግብ ማቅረብ እና የማግባት ሂደቱን ማገዝ ከአሠልጣኙ የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። በዛሬው ጨዋታ በአፄዎቹ በኩል እዮብ ማትያስ፣ አምሳሉ ጥላሁን እና ይሁን እንደሻው በጉዳት አይሰለፉም። ዋና አሠልጣኙ ውበቱ አባተ፣ ጋቶች ፓኖም እና ምኞት ደበበ ደግሞ በቅጣት ከሥብሥቡ ውጭ ናቸው ተብሏል።
የዛሬው ጨዋታ የፋሲል ተጋጣሚ መቻል የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ንግድ ባንክ በባሕር ዳር ከተማ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ወደ ዋንጫው ፉክክር ይበልጥ እንዲጠጋ ሙሉ ነጥብ አስፈላጊው ነው። የመቻልን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ስንቃኝ በእንቅስቃሴው የተሻለ ነበር። በአራት ጨዋታዎች 10 ግቦች ያስቆጠረ ውጤታማ የአጥቂ ክፍል አለው።
ቡድኑ በፍጥነት ማጥቃት ቢችልም ተጋጣሚው ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ያለው እና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ መኾኑ ከፋሲል የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንዳልኾነ መገመት አያዳግትም። መቻል በዛሬው ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት በመሐል እና በመስመር ከሚሰነዝራቸው ጥቃቶች በተጨማሪ የግብ ዕድሎች መፍጠሪያ ሌሎች መንገዶችን ማብዛት እጅግ አስፈላጊው ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ሸር ካምፓኒ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ ስድስት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው። መቻል በበኩሉ በሦስት ጨዋታዎች አሸንፏል። በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል። በሌላ በኩል ምሽት 12 ሰዓት በ37 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ አምስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይጫወታሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!