ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ በጀርመን የብዙ እግር ኳስ አፍቃሪያን የዐይን ማረፊያ እንደሚኾን ይጠበቃል። ውድድሩ 24 ብሔራዊ ቡድኖችን ያፎካክራል። በግል ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ኪሊያን ምባፔን፣ ሀሪ ኬን እና ቤሊንግሀምን የመሳሰሉ ኮከቦች የውድድሩ ድምቀቶች ናቸው። እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቱጋል እና ጀርመንን የመሳሰሉ ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ አንደ ቡድን ይጠበቃሉ። የአውሮፓ ሀገራት አህጉራዊ ውድድር እንዲኖራቸው ከወጠኑ ለአንድ ክፍለ ዘመን የተጠጋ ጊዜ አልፏል። ነገር ግን በሀሳብ ደረጃ አንድ ኾነው ወደ ተግባር የገቡት በእነሱው ዘመን በ1958 ነው።
ውድድሩ” ሀ” ብሎ የተጀመረው ደግሞ እ.አ.አ 1960 በፈረንሳይ ፓሪስ ነው -አንደ ዩሮ ኒውስ መረጃ። በወቅቱ አራት ብሔራዊ ቡድኖች ተሳትፈዋል። አዘጋጇ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ አሁን ከዓለም ካርታ ላይ የማትገኘው ዩጎዝላቪያ እና የያኔዋ ሶቪየት ሕብረት /የአሁኗ ሩሲያ/ ተሳታፊ ሀገራት ነበሩ።
በወቅቱ እንግሊዝን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ከምሥራቁ የአህጉሩ ክፍል ጋር ባለቸው የርዮዕተ ዓለም ልዩነት ምክኒያት በውድድሩ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። ውድድሩን ሶቪየት ሕብረት በማሸነፍ የመጀመሪያ ሀገር ናት። ለፍጻሜ ከዩጎዝላቪያ ጋር የተጫወተችው ሶቪየት 2ለ 1 በማሸነፍ ነው የዋንጫ ባለቤት የኾነችው።
በዚህ መንገድ የተጀመረው የአውሮፓ ሀገራት የእግር ኳስ ውድድር ከስያሜ ጀምሮ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር እያሳደገ እዚህ ደርሷል። በአራት ሀገራት የተጀመረው ውድድር አሁን 24 ሀገራት ያሳትፋል። 55 የአህጉሩ ሀገራት ደግሞ የተሳታፊነት ቦታን ለማግኘት የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ። የአውሮፓ ዋንጫ በአራት ዓመት አንዴ ይካሄዳል።በውድድሩ ታሪክ የዘንድሮው የጀርመኑ ድግስ 17ኛው ነው። ከዚህ በፊት በተደረጉ 16 ውድድሮች 10 የተለያዩ ሀገራት የዋንጫ ባለቤት መኾናቸውን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያሳያል።
ጀርመን እና ስፔን የውድድሩ ስኬታማዎቹ ሀገራት ናቸው። እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል። ፈረንሳይ እና ጣሊያን ሁለት ሁለት ጊዜ የአውሮፓ የእግር ኳስ ቁንጮ በመኾን ይከተላሉ። በውድድሩ ታሪክ የእንግሊዝ ዋንጫውን አንስቶ አለማውቅ በአህጉሩ ብቻ ሳይኾን በዓለም ቀዳሚ ሊግ አላት ለሚባለው ሀገር እንደ እርግማን ተቆጥሯል። የማይረሳው የኢኔስታ እና ዣቪን ምትሀት፣ የማይሰበረውን የእነ ሰርጅዮ ራሞስ እና አይከር ካሲያስ የኋላ ደጀንነትን ለዓለም ያስመለከተው “ወርቃማው የስፔን ትውልድ” ዋንጫውን በተከታታይ በማንሳት እስካሁን ብቸኛው ሀገር ነው። ስፔን የ2008 እና 2012ቱን የአውሮፓ ዋንጫ ነው በተከታታይ ያነሳችው።
የአውሮፓ ዋንጫው በተለያዩ ጊዜያት ምርጥ ተጫዋቾችን አሳይቷል። ጊቭ ሚ ስፖርት የተሰኘ የመረጃ ምንጭ ከእነዚህ ሁሉ ተጫዋቾች ቀዳሚው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው ይላል። ሮናልዶ በአምስት የአውሮፓ ዋንጫ ተሳትፏል። ለስድስተኛው ደግሞ ጀርመን ላይ ይገኛል።በውድድሩ በ25 ጨዋታዎች በመሰለፍ ብቸኛው ተጫዋች ነው። 14 ግቦችንም በማስቆጠር ሌላ ብቸኛ የሚያስብል ታሪክ ጽፏል። እነዚህን ክብረወሰኖች ይበልጥ ከፍ ለማድረግም ሜዳውም ፈረሱም ጀርመን ላይ ተዘጋጅቶለታል። ሮናልዶ አንድ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ ከሀገሩ ጋር ማሸነፉ ይታወሳል።
ከሮናልዶ በመቀጠል በአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጦች አንድሬስ ኢኔስታ፣ ዚነዲን ዚዳን እና ሚሼል ፕላቲኒ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ በጀርመን እ.አ.አ ከሰኔ 14 አስከ ሀምሌ 14 ይካሄዳል። ይህ ውድድር ምናልባትም እንግሊዝ ዐይነ ጥላዋን የምትገፍበት፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የመጨረሻ የአውሮፓ ዋንጫን የሚያከናውንበት፣ ምባፔ፣ ቤሊንግሀም እና ሙሴላን የመሳሰሉ ኮከቦች የሚደምቁበት ሊኾን እንደሚችል በስፍት ተገምቷል። መጨረሻ ላይ የሚኾነውን ለማየት ግን ዓለም ለ30 ቀናት ጀርመን ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!