በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይመለሳል፡፡

0
220

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በነበረበት ጨዋታ ምክንያት ተቋርጦ መሰንበቱ ይታዎሳል። ከዚህ መልስ ታዲያ ዛሬ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባሕር ዳር ከተማ እንዲሁም 12 ሰዓት ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ ጨዋታዎችን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደርጋሉ።

ባሕር ዳር ከተማ ዋንጫውን ለማንሳት የላቀ ዕድል ይዞ የሚቀርበውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል። የጣናው ሞገድ (ባሕር ዳር ከተማ) በ45 ነጥብ በሰንጠረዡ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ የሊጉ መሪ ነው። ወደ ጨዋታው ስንመለስ ረዘም ላሉ ጊዜያት በዘለቀ ሽንፈት አልባ ጉዞ ላይ የሚገኙት ባሕር ዳር ከተማዎች በዛሬው ጨዋታም ለተጋጣሚያቸው ብርቱ ፈተና እንደሚኾኑ ይጠበቃል፤ በሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክክሩ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በጣና ሞገዶቹ በኩል የቸርነት ጉግሳ እና የያሬድ ባየህ መመለስ መልካም ዜና ሲኾን ከሙጅብ ቃሲም በስተቀር ሌሎቹ የቡድን አባሎች ለጨዋታው ዝግጁ መኾናቸው ታውቋል። በ56 ነጥብ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋንጫውን ለማንሳት የላቀ ዕድል ይዞ ነው የሚቀርበው። በሊጉ መሪ እና በሁለተኛነት በሚከተለው መቻል መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት የአምስት ነው። ይህን ልዩነት አስጠብቀው ለመውጣት ነው ባንኮች የሚጫወቱት። ይሁን እና ከባሕር ዳር ከተማ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሙሉ ቋሚ ተሰላፊዎችን ይዞ ይገባል ነው የተባለው። በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። ሠራተኞቹ በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል። ሠራተኞቹ በሊጉ የመትረፍ ዕድላቸው በእጃቸው ቢገኝም በተከታታይነት ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት ከቅርብ ተቀናቃኛቸው ሻሸመኔ ከተማ መሻሻል ጋር ተደምሮ ስጋት ውስጥ ይከታቸዋል።

ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በዛሬው ዕለት ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብቻ አስር ግቦች ካስቆጠረው የቡና ጠንካራ የፊት መስመር ለሚገጥመው ፈተና የሚቋቋምበት መንገድም የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብ ያላገናኘው የቡድኑ የፊት ጥምረት በጨዋታው የሚኖረው ብቃት ከወራጅ ቀጣናው ለመሸሽ ለሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ ነው።

በ44 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የደረጃ መሻሻልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡናማዎቹ 10 ግቦች ባስቆጠሩባቸው ተከታታይ ሦስት ድሎች የአፈፃፀም ክፍተታቸውን ቀርፈዋል። ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጠንካራ ፍልሚያ እንደሚኖረው በሚጠበቀው በዛሬው ጨዋታ ፈታኝ የማጥቃት አደጋዎች ይገጥሙታል ብሎ ለመገመት ቢያዳግትም በአንዳንድ መርሐ-ግብሮች የሚታዩበትን ያልታሰበ የመከላከል ድክመት ማረም ይጠበቅበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ተጋጣሚያቸው ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅ ወሳኝ ነጥብ ፍለጋ ላይ ያለ መኾኑም ጠንካራ ተፎካካሪ ኾኖ የሚቀርብበት ዕድልም አለ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ በዛሬው ጨዋታ ላይ በሕመም ምክንያት የማይኖር ተጫዋች ነው።

በወልቂጤ ከተማ የአምስት ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ክለቡን የከሰሱት በርካታ ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር አለመገኘታቸውን ተከትሎ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲኾኑ ይህም ወልቂጤ ከተማ ጨዋታን ያለ ሁለቱ ተቀዳሚ ግብ ጠባቂዎቹ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ይኾናል ሲል ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል።

ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ56 ነጥብ ይመራዋል። መቻል በ51 ነጥብ ይከተላል። ባሕር ዳር በ45 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወልቂጤ በ16 ነጥብ፣ ሻሸመኔ በ14 እንዲሁም ሀምብሪቾ በስምንት ነጥብ የመጨረሻዎቹን ደረጃ ይዘዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here