ክርስቲያኖ ሮናልዶ የአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጡ ተጨዋች ተባለ፡፡

0
288

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአምስት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና የብዙ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጡ ተጨዋች ነው ተብሏል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ 14 ግቦችን በማስቆጠር የክብረ ወሰን ባለቤት የኾነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በታሪክ ከእሱ የሚቀድም ተጫዋች የለም ነው የተባለው፡፡

ለስድስተኛ ጊዜ በአውሮፓ ዋንጫ ለመሳተፍ ከሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር እየተዘጋጀ ያለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሌሎች ታሪኮችን የመጻፍ ሰፊ ዕድሎች ፊት ለፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ዘ ሰን ፉት ቦል ከደጋፊዎች ሠበሠብኩት ባለው ድምጽ በአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጥ 20 ጨዋታዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
“ክብረወሰኖች ይከተሉኛል እንጂ አልከተላቸውም” የሚለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ደግሞ ከደጋፊዎች በተሠበሠበው ድምጽ የምንጊዜውም ምርጥ ተጫዋች በመባል በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ምርጡ ተጫዋች ዜነዲን ዚዳን ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ባለ ታሪክ ተጫዋች ቦቢ ቻርሊተን ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በእንግሊዝ የ”ሰርነት” ማዕረግ የተሰጡት ቦቢ ቻርሊተርን በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ታላቅ ስም አላቸው፡፡ እኝህ ታላቅ የእግር ኳስ ተጫዋች አሁን ላይ በሕይወት የሉም፡፡

ሌላኛው እንግሊዛዊ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም ከምንግዜም ምርጥ 20 የአውሮፓ ዋንጫ ተጫዋቾች መካከል አራተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ የዘመናዊ እግር ኳስ አቀንቃኝ እንደኾኑ የሚነገርላቸው ኔዘርላንዳዊ ሕዋን ክራይፍ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ፈረንሳዊው ቴሪ ሄነሪ ስድስተኛ ደረጃን ሲይዝ ጀርመናዊ ባለ ታሪክ ተጨዋች ፍራንዝ አንቶን ቤክንባውር ሰባተኛው የምንጊዜም ምርጡ ተጫዋች ተሰኝተዋል፡፡

እንግሊዛዊያኑ ሀሪ ኬን፣ ፖል ጆን ካስኮኝ፣ አለን ሽረር፣ ስቴቨን ጄራርድ ከስምንተኛ እስከ አሥራ አንደኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ ኔዘርላንዳዊው ማርኮ ቫንባስተን ከምርጥ 20 ተጨዋቾች መካከል 12ኛው ምርጡ ተጫዋች ተብሏል፡፡ ጣልያናዊው ምርጡ ተጫዋች ፓውሎ ማልዲኒ ደግሞ አሥራ ሦስተኛው ምርጡ ተጨዋች ተሰኝቷል፡፡

ዴንማርካዊ የቀድሞው ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል፣ ኔዘርላንዳዊው ሩድ ጉሌት፣ ጀርመናዊው ገርድ ሙለር፣ ሲውዲናዊው ዝላታን ኢቭራሄምሙቪች፣ ዌልሳው ጋሬዝ ቤል፣ ክሮሽያዊው ሉካ ሞድሪች እና ስፔናዊው አንድሬስ ኢንስታ ከ14 እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጥ 20 ተጨዋቾች ተብለው ከተመረጡት መካከል ሦስት ተጫዋቾች በ2024 በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ይጫወታሉ፡፡

በ2020 የጀርመን አውሮፓ ዋንጫ የሚጫወቱት ከምንጊዜም ምርጥ 20 ተጫዋቾች መካከል ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሃሪ ኬን እና ሉካ ሞድሪች ናቸው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here