ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርባ ምንጭ የእግር ኳስ ቡድን ወይም አርባ ምንጭ ከተማ በቅጽል ስሙ አዞዎቹ ጨዋ ቡድን፣ በኅብረ ቀለም ባሸበረቁ እና የወገብ ዳንሰኛ እና ፍቅርን በሚሰብኩ ደጋፊዎቹ የሚታወቅ ቡድን ነው። ሕብረትን እና ፍቅርን በሚሰብኩ ሕብረ ዝማሬዎችም ይለያሉ።
አርባ ምንጭ ከተማ ባለፉት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው የአሠልጣኞች ተደጋጋሚ ለውጥ በማድረግ እና አሥተዳደራዊ አሠራሮችን በማስተካከል ለዓመታት በውድድር ሲታገል ቆይቷል። ከተከታታይ ዓመታት ትግል በኋላም ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅሏል። ዘንድሮ የአርባ ምንጭ ከነማ እግር ኳስ ቡድን በሚካፈልበት ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሁለት በቀጣይ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ መሳተፍ የሚያስችለውን ነጥብ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት አሳክቷል።
የቡድኑ አሠልጣኝ በረከት ደሙ ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት ”በጋራ መሥራታችን እና የደጋፊዎቻችን አቅም መጠቀማችን ለስኬት አብቅቶናል” ብለዋል። በቀጣይም ክለቡን በዘላቂነት ውጤታማ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንደሚሠሩም ተናግረዋል። በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ በነበረው የውድድር ዓመት ብዙ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም የደጋፊዎች ድጋፍ በአግባቡ መጠቀማቸው ለውጤት እንዳበቃቸው አሠልጣኙ ለአሚኮ ተናግረዋል።
በሀዋሳ አንደኛ ዙር ውድድር አንድም ጨዋታ ሳይሸነፉ 10 አሸንፈው 3 አቻ በመውጣት ሊጉን መርተው ማጠናቀቃቸውን የገለጹት አሠልጣኙ በአዲስ አበባው ሁለተኛ ዙርም የደጋፊዎችም ጥረት ታክሎበት ውጤት ብቻ ሳይኾን ጨዋታም አሳይተው የሚገባቸውን ውጤት አግኝተው የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ያለፈውን የውድድር ዓመት ድክመት በሚገባ በመገምገም ወደ ውድድር መግባታቸው እና ከታችኛው ጀምሮ እስከ ክለቡ የቦርድ አመራር ድረስ በጋራ መሥራታቸው ሌላኛው የአርባ ምንጭ ስኬት ምንጭ መኾኑን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አስጨናቂ ዳዊት ተናግረዋል። አሠልጣኙ እና ሥራ አስኪያጁ ክለቡ በሊጉ ውጤታማ ኾኖ እንዲቆይ በቡድኑ ስብስብ እና በገቢ ደረጃ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
አሠልጣኝ በረከት ቡድኑ ጠንካራ እና በሊጉ ተፎካካሪ እንዲኾን የሚያስችል የቡድን ግንባታ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ስህተቶችን ባለመድገም እና ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማድረግ ውጤታማ ለመኾን ማለማቸውንም ተናግረዋል። ሥራ አስካያጁ አስጨናቂ ዳዊት በበኩላቸው ቡድኑ የሚንቀሳቀሰው በመግሥት ድጎማ መኾኑን እና በቀጣይ ግን ሕዝቡ በአባልነት ክፍያ እና በሌሎች መንገዶችም ቡድኑን እንዲደግፍ እቅድ ይዘው እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
በ2016 የውድድር ዓመት በምድብ አንድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፤ በምድብ ሁለት ደግሞ አርባ ምንጭ ከነማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መቀላቀላቸው ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!