17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ከቀናት በኋላ በጀርመን ይጀመራል። 24 ሀገራት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ሀገራት የዋንጫ ባለቤት ለመኾን ዝግጅት እያደረጉ ነው። በዚህ መሀል ዋንጫውን ማን ያነሳል የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው። ኦፕታ የመረጃ ትንተናን በመጠቀም እግርኳሳዊ ግምቶችን በመስጠት ይታወቃል። የአውሮፓ ዋንጫን ማን ያሸንፋል የሚለውን ግምት አስቀምጧል። ከተሳታፊ 24 ሀገራት መካከልም የሰባቱን የዋንጫ የማንሳት እድል በመቶኛ ገምቷል።
ዋንጫ የማግኘት ዕድል አላቸው ከተባሉ ሀገራት መካከል ቤልጀም 4 ነጥብ 7 በመቶ ያሸናፊነት ግምት በማግኘት ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ያለፈው የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት ጣሊያን 5 በመቶ የዋንጫ ዕድል ተሰጥቷታል። ኔዘርላንድስ ከጣሊያን ከፍ በማለት 5 ነጥብ 1 በመቶ ዋንጫ በማግኘት ግምት ስድስተኛዋ ለዋንጫው ግምት የቀረበች ሀገር አድርጓታል ኦፕታ።
በኦፕታ ግምት መሠረት የሮናልዶዋ ፖርቱጋል 9 ነጥብ 2 በመቶ ዋንጫ የማሸነፍ ዕድል አላት። ፖርቱጋል በተለይ በአጥቂ እና መሀል ሥፍራ ያላት የቡድን ጥራት ለተጋጣሚዎቿ የራስ ምታት ነው። በአጥቂ ክፍል ከአንጋፋው ክርስቲያኖ ሮናልዶ አስከ ወጣቱ ኮከብ ራፋኤል ሊያው የሚቀናበት ሥብሥብ ይዟል። በመሀል ክፍል ደግሞ ቡርኖ ፈርናንዴስ እና በርናንዶ ሲልቫን የመሰሉ ያለቀ ኳስ አቅራቢዎችን ይዟል። ቡድኑ 33 ነጥብ 6 በመቶ ግማሽ ፍጻሜ፣ 18 በመቶ ፍጻሜ ላይ የመድረስ እና 9 ነጥብ 2 በመቶ ዋንጫ የማንሳት ቅድመ ግምት አግኝቷል።
በኦፕታ ግምት መሰረት ዋንጫውን የማግኘት 9 ነጥብ 6 በመቶ ግምት ያገኘችው ሀገር ስፔን። ስፔን በወርቃማ ትውልዷ በአውሮፓ እና ዓለም ዋንጫ ከነገሰች በኋላ ለትልቅ ክብር አልበቃችም። ሀገሪቱ ኮከቦችን የማፍራት ችግር ባይገጥማትም ዣቪ እና ኢኔስታን፣ ራሞስ እና ፒኬን በልካቸው የሚተኩ ተጫዋችን ግን አላገኘችም። በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ በአትሌቲኮ ማድሪዱ አልቫሮ ሞራታ ግብ አስቆጣሪነት እና በሲቲው ሮድሪ የመሀል ክፍል ጥንካሬን ከወጣቶች በማዋሀድ ዋንጫውን እያሰበች በርሊን ትከትማለች። 9 ነጥብ 6 በመቶ ዋንጫ የማግኘት ቅድመ ግምትም ተሰጥቷታል።
አዘጋጇ ጀርመን የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ በደጋፊዋ ፊት ለማንሳት ያገኘችው ቅድመ ግምት 12 ነጥብ 4 በመቶ ነው። ይህ ቁጥር ጀርመንን ሦስተኛዋ ለዋንጫ ቅደመ ግምት ያገኘች ሀገር አድርጓታል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከ2014 የዓለም ዋንጫ በኅላ ከደካማ እንቅስቃሴው መንቃት አልቻለም። ዋንጫውን ከአነሳ ከ10 ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ሲቆጠር ከዚያ ወዲህ በዓለምም ይሁን በአውሮፓ ዋንጫ ለተጋጣሚዎቹ ቀሎ ታይቷል።
ያም ኾኖ አሁን በሀገራቸው የሚደረገው እና ከቀናት በኋላ የሚጀምረው የአውሮፓ ዋንጫ የእግርኳሳቸውን እንቆቅልሽ እንዲፈታ ይፈልጋሉ ጀርመናውያን። የባለፉት ጊዚያት ቁጭት ብሔራዊ ቡድኑን ለድል ይበልጥ እንደሚያነሳሳውም ይጠበቃል። ኦፕታ 12 ነጥብ 4 በመቶ ዋንጫ የመውሰድ ቅድመ ግምትም ሰጥቷቸዋል።
ፈረንሳይ ባለፋት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ድንቅ እንቅስቃሴን ያደረገ ብሔራዊ ቡድን ባለቤት ናት። በሩሲያው ድግስ ዋንጫን ስታነሳ ኳታር ላይ ደግሞ በአርጀንቲና ተሸንፋ የብር ሜዳሊያ ባለቤት መኾኗ ይታወሳል። በዓለም ላይ ያሳየችው የበላይነት በአውሮፓ ዋንጫ ግን አልተደገመም። ብዙ የብሔራዊ ቡድን ታጫዋቾች ፍላጎትም የአውሮፓ ዋንጫን በማንሳት ከሀገራቸው ጋር የአውሮፓ እና የዓለም አሸናፊ የሚል ግለ ታሪክ መጻፍ ነው። ሜዳ ላይ በኪሊያን ምባፔ የሚመራው የፈረንሳይ ሥብሥብ በየቦታው ይሄ ይጎለዋል የሚባል ዓመል አይወጣለትም። 19 ነጥብ 1 የዋንጫ ባለቤትነት ግምት በማግኘትም ሁለተኛው ለዋንጫ ተጠባቂ ቡድን ነው።
ኦፕታ ዘንድሮ የአውሮፓ ዋንጫን ታነሳለች ብሎ በቀዳሚነት ያስቀመጣት ሀገር በትልልቅ ውድድሮች ጉልበቷ የሚዝለው፤ ነገር ግን በየጊዜው ኮከቦችን የማፍራት ችግር የሌለባት እንግሊዝን ነው። የእግር ኳስ ፈጣሪ ነኝ የምትለው እንግሊዝ የአውሮፓ ዋንጫን አንስታ አለማወቋ ትልቁ ጠባሳዋ ነው። ውድድሩ በደረሰ ቁጥር በያዘቻቸው ተጫዋቾች ጥራት ለዋንጫ ቀድማ የምትገመተው ይቺው ሀገር ብዙ ጊዜ በተመዘነችው ልክ አልተገኘችም። ባለፉት ስድስት እና ሰባት የአውሮፓ ዋንጫዎች እንግሊዝ ለዋንጫው ተገመተች ነገር ግን ጀርመን፣ ስፔን፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ ዋንጫ በሉ ሲል ቢቢሲ መጻፉም ለዚህ ማሳያ ነው።
በእንግሊዝ የአሁን ሥብሥብ ውስጥ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ሀሪኬን፣ በስፔን የመጀመሪያ ቆይታው በድል የተንቆጠቆጠው ጁዲ ቢሊንግሃም፣ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ፊል ፎደንን ጨምሮ በርካታ ኮከቦች ይገኛሉ። በኦፕታ ግምት መሠረት የጀርመኑን የአውሮፓ ዋንጫ ለማግኘትም ቀዳሚዋ ሀገር እንግሊዝ ናት። 19 ነጥብ 9 በመቶ ደግሞ ዋንጫውን ለማግኘት ያላት ዕድል ነው ብሏል።
እንግሊዝ የእግር ኳሱ ዓለም ያደነቃቸው ተጫዋቾችን በየጊዜው አፍርታለች። በየጊዜው በኮከቦች የተሞላ ብሔራዊ ቡድንም ለዓለም አሳይታለች። ነገር ግን በአውሮፓ ዋንጫ ያነገሳት ተጫዋችም ቡድንም በታሪክ የለም። ባለፈው የአውሮፓ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሳ በጣሊያን መሸነፏ ይታወሳል። ብዙ እየተባለለት ያለው የአሁኑ ሥብሥቧስ የት ይደርስ ይኾን የሚለውም ይጠበቃል። የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 14 ተጀምሮ ሐምሌ 14 በርሊን ላይ ይጠናቀቃል።
በአስማማው አማረ