ኢትዮጵያ ወሳኝ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች።

0
320

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2026 በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ አዘጋጅነት የሚካሄደው 23ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት ይሳተፉበታል ሲል ፊፋ ማስታዎቁ ይታወሳል፡፡ 45 የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በዘጠኝ ምድብ ተደልድለውም ጨዋታቸውን በማድረግ ዘጠኝ ሀገራት አላፊ ይኾናሉ ነው የተባለው፡፡

እኛም ካፍ ኦን ላይንን መነሻ አድርገን ዛሬ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ቃኝተናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ከጊኒ ቢሳው ጋር ዛሬ ያደርጋል። የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ “በስታዲዮ ናሲዮናል 24 ዲ ሴቴምብሮ” ሜዳ ላይ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከግብጽ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን እና ጅቡቲ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን እያደረገች ትገኛለች።

ቡድኑ በምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ በቡርኪናፋሶ 3 ለ 0 ሲሸነፍ ከሴራሊዮን ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቶ በ1 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ የጊኒ ቢሳው ቡድን በ4 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጨዋታውን ከቤኒን የተመደቡት ጂንዶ ልዊስ በዋና ዳኝነት ይመሩታል፡፡ የሀገራቸው ልጆች አይማር ኤሪክ፣ ጆ ኮርቴል እና ሙሐመድ ኢሳ ረዳቶቻቸው ይኾናሉ፡፡ ጋምቢያዊው ጃሜ ባካሪ ደግሞ የጨዋታው ኮሚሽነር ይኾናሉ ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ጨዋታውን ፊፋ ፕላስ በቀጥታ ስርጭት ያስተላልፈዋል ተብሏል። ምድብ አንድን ግብጽ በስድስት ነጥብ እየመራች ሲኾን ቡርኪናፋሶ ጊኒ ቢሳውን በግብ ክፍያ ብቻ በልጣ በአራት ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በዚሁ ምድብ ትናንት በተደረገ ጨዋታ ሴራሊዮን ጅቡቲን 2 ለ 1 በማሸነፍ ነጥቧን ወደ 4 ከፍ አድርጋለች።

በሌላ ጨዋታ ምድብ አንድን በስድስት ነጥብ የምትመራው ግብጽ ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ 75 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው የካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሁለተኛነት የምትከተላትን ቡርኪና ፋሶ ትገጥማለች፡፡ “ፈርኦኖች” በማጣሪያው ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ለማጣጣም ነው የሚጫወቱት፡፡ ቡርኪናዎች ደግሞ አሸንፈው ደረጃቸውን ለማስጠበቅ ይጫወታሉ፡፡

በምድብ ሁለት ሴኔጋል ዲሞክራቲክ ኮንጎን ታስተናግዳለች፡፡ ምድቡን ሴኔጋል በአራት ነጥብ ስትመራው ሱዳን በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ናት፡፡ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በሦስት ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ በጨዋታው ሴኔጋል የአንደኝነት ደረጃዋን አስጠብቃ ለመቀጠል ዲሞክራቲክ ኮንጎዎቹ የሁለተኛነት ደረጃን ለመያዝ ይጫወታሉ ነው የተባለው፡፡

ምድብ ሰባትን በስድስት ነጥብ የምትመራው አልጄሪያ በሦስት ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችውን ጊኒን በ”ኔልሰን ማንዴላ” ስታዲየም ትገጥማለች፡፡ በአሠልጣኝ ቭላድሚር ፔትኮቪች የሚመሩት የ”በረሃ ቀበሮዎቹ” መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ይጫዎታሉ፡፡ ነገር ግን የጊኒው አሠልጣኝ ካባ ዲያዋራ ቡድናቸው አልጄሪያን እንደ ሚያሸንፍ “እርግጠኛ ነኝ ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

ማሊ ከጋና ሌላው ዛሬ የሚደረግ ጨዋታ ነው፡፡ በምድብ ስምንት አራት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ማሊ በሦስት ነጥብ አምስተኛ ላይ ያለችውን ጋናን ታስተናግዳለች፡፡ ይህ ጨዋታ ከባድ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ተጠብቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here