ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን በመወከል በጃፓን ሀገር ኮቤ ከተማ በዓለም ፓራ ኦሎምፒክ ሻምፒዮና ላይ ተወዳድራ የዓለም ሪከርድን በመስበር አሸናፊ ለኾነችው እና የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኘችው አትሌት ያየሽ ጌቴ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር አቀባበል አድርጓል፡፡
በከተማዋ የታዳጊ ፕሮጀክት ሠልጣኝ የኾነችው እና በጃፓን ኮቤ ከተማ በተካሄደው የዓለም ፓራ ኦሎምፒክ ሻምፒዮና በ1ሽህ 500 ሜትር ተወዳድራ የዓለም ሪከርድን በመስበር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችውን እና ሰንደቅ ዓላማው ክፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረገችው አትሌት ያየሽ ጌቴ የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እና የስፖርት ቤተሰቡ በተገኘበት አቀባበል ተደርጓላታል፡፡
በአቀባበሉ እና በዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን አትሌት ያየሽ ጌቴ በዓለም ስፖርት አደባባይ አሸናፊ በመኾን የሀገሯን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲታይ በማድረግ ለሕዝቡ ኩራት መኾኗን ተናግረዋል፡፡ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ በአካባቢው ብዙ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ያሳየች እና የቤት ሥራ የሰጠች ናት ብለዋል፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ ስፖርቱን ለማሳደግ እና ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የገለጹት ከንቲባ ደሴ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ እየሠሩ ያሉ አካላት በሚፈለገው አግባብ ስፖርቱን ለማሳደግ እና ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ እሸቱ ውለታው በከተማ አሥተዳደሩ ስፖርቱን ለማሳደግ እና ስፖርተኞችን ለማፍራት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በታዳጊ ፕሮጀክት ታቅፋ በመሠልጠን ላይ ያለችው የፓራ ስፖርት ተወዳዳሪዋ አትሌት ያየሽ ጌቴ ውጤታማ መኾኗንም ተናግረዋል፡፡
አትሌቷ ከዚህ በፊትም በዱባይ እና በቱኒዚያ በተካሄዱ ውድድሮች ላይ አሸናፊ መኾኗን ጠቁመው ጠንካራ እና በቀጣይም ትልቅ ተስፋ የተጣለባት አትሌት መኾኗን ተናግረዋል፡፡ ከአትሌት ያየሽ በተጨማሪ ብቃት ያላቸው ሌሎችም አትሌቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ተወዳዳሪ እና አሸናፊ እንዲኾኑ ለማድረግ እገዛ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በሚፈለገው አግባብ ስፖርተኞችን ለማፍራት እና ስፖርቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ መላው ኅብረተሰብም ስፖርቱን ለማሳደግ እና ሕዝብ እና ሀገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ለማፋራት የድርሻውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአትሌት ያየሽ ጌቴ አሠልጣኝ ክንዱ ሲሳይ አትሌቷ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ እንድትኾን ጠንክረው መሥራታቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በላይ ውጤት ለማምጣት ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡ አቅም እና ችሎታ ያላቸው ሌሎችም አትሌቶች መኖራቸውን ጠቅሶ ስፖርተኞችን በበቂ ሁኔታ ለማፍራት ከተማ አሥተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ እና እገዛ እንዲያደርግም ጠይቋል፡፡
አትሌት ያየሽ ጌቴ ላስመዘገበችው ትልቅ ውጤት እና ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዕውቅና እና ስጦታ ተበርክቷላታል፡፡ የደብረታቦር ከተማ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው አትሌት ያየሽ ጌቴ በቀጣይ በፈረንሳይ ሀገር ፓሪስ ከተማ ላይ በሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክላ እንደምትወዳደር ተገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!