ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ በጥንታዊቷ ሀገር ግሪክ በአቴንስ ከተማ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ውድድሮች ከቻምፒዮንስ ሊግ እና ኢሮፓ ሊግ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኢሮፓ ኮንፈረስ ሊግ ዛሬ የፍጻሜ ጨዋታው ይከናወናል፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ ከጣሊያኑ ፍዮረንቲና ጋር ይገናኛሉ፡፡
ጨዋታው 32 ሺህ 500 ደጋፊዎችን በሚይዘው የግሪኩ ኦፓፕ አረኔና ( ኤጂያ ሶፊያ) ስታዲዬም ይካሄዳል፡፡ ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይደረጋል፡፡ የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ በግማሽ ፍጻሜው የእንግሊዙን አስቶን ቪላ 6 ለ 2 በኾነ የደርሶ መልስ ውጤት አሸንፎ ለፍጻሜ መድረሱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ፊዮረንቲና በበኩሉ ክለብ ብሩጅን 4 ለ 3 በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፎ ነው ለፍጻሜ የደረሰው፡፡ ዘ ስታንዳርድ እንደዘገበው የጣሊያኑ ፊዮረንቲና ለተከታታይ ዓመታት ለፍጻሜ ደርሷል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በፍጻሜው ጨዋታ በዌስትሐም ዩናይትድ ተሸንፎ ዋንጫውን መነጠቁን አስታውሰዋል፡፡ ፊዮረንቲና በድጋሚ ለፍጻሜ በደረሰበት ጨዋታ ዋንጫውን የግሉ ለማድረግ ይፋለማል፡፡
የግሪኳ ጥንታዊት ከተማ አቴንስ የፍጻሜውን ድግስ ደግሳለች፡፡ የጥንታዊቷ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፍ ለሁለት እንደሚከፈል ይጠበቃል፡፡ በሀገሩ ግሪክ የሚጫወተው ኦሎምፒያኮስ በርካታ ደጋፊዎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፤ ነገር ግን የምንጊዜም ባላንጣው የኤኢኬ አቴንስ ደጋፊዎች ፊዮረንቲናን ሊደግፉ እንደሚችሉም ዘ ስታንዳርድ በዘገባው አመላክቷል፡፡
ኦሎምፒያኮስ በአውሮፓ ውድድሮች የፍጻሜ ጨዋታ በሀገሩ ያደርጋል፡፡ ከአሁን ቀደም ባየርን ሙኒክ በ2011/12 በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ እና በኦሎምፒክ ማርሴል በ2017/18 በኢሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎች በሀገራቸው ተጫውተዋል፡፡ ነገር ግን በሀገራቸው የፍጻሜ ጨዋታ የተጫወቱት ሁለቱ ክለቦች ተሸንፈዋል፡፡ ዛሬ ኦሎምፒያኮስ በሀገሩ ይሸነፋል ወይስ ድል ያደርጋል የሚለው ይጠበቃል፡፡
ኦሎምፒያኮስ በምንግዜም ባላንጣው ኤኢኬ አቴንስ ሜዳ ታሪክ ለመሥራት ይጫዎታል ነው የተባለው፡፡ ፊዮረንቲናዎች ደግሞ ባለፈው ዓመት የደረሰባቸውን ሽንፈት ለማካካስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!