ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በቀጣይ የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ ቡድኑን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡ አሠልጣኙ ቡድኑን እንደሚለቁ ያሳወቁት ሲቲ በኤፍ.ኤ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ በማንቸስተር ዩናይትድ 2 ለ 1 በተሸነፉ ማግሥት ነው፡፡
ስፔናዊው የ53 ዓመቱ ፔፕ ጋርዲዮላ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ በ2023/2024 የውድድር ዘመን ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫ እንዲወስድ አድርገውታል፡፡ ሰውየው በቡድኑ ቆይታቸው የፕሪሚየር ሊግ፣ የካራባኦ ፣ ኤፍ.ኤ ፣ የኮሙኒቲ ሺልድ፣ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የሱፐር ካፕ እንዲሁም የዓለም ክለቦች ዋንጫን በማሸነፍ ስኬታማ አሠልጣኝ ናቸው፡፡
ጋርዲዮላ ለዴይሊ ሜይል “እኔ ማንቸስተር ሲቲ ውስጥ ከመቆየት ይልቅ ለመልቀቅ ተዘጋጅቻለሁ” ሲሉ መናገራቸውን ዘግቧል፡፡ አሠልጣኝ ጋርዲዮላ ኢትሃድን የተቀላቀሉት በ2016 መኾኑን ያስታወሰው ዴይሊ ሜይል ማንቸስተር ሲቲ ሰውየውን የኮንትራት ማራዘሚያ ውል ለማስፈረም ቢፈልግም አሠልጣኙ ግን “የሲቲ የቆይታ ጊዜየ በሚቀጥለው ዓመት ያበቃል፤ እኔም አዲስ ነገር ለማግኘት ከኢትሃድ መውጣቴ አይቀርም” በማለት በቀጣይ ዓመት ከሲቲ ሊለቁ እንዳሰቡ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!