ክላውዲዮ ራኒየሪ ከአሠልጣኝነት በጡረታ ሊሰናበቱ ነው፡፡

0
231

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክላውዲዮ ራኒየሪ ከአሠልጣኝነት ሥራቸው በጡረታ በክብር ሊሰናበቱ ነው፡፡ ራኒየሪ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው የአራት ሀገራትን ቡድኖች አሠልጥነዋል፡፡ በእንግሊዝ ቸልሲ፣ ፉልሃም፣ ሌስተር ሲቲን፣ በፈረንሳይ ሞናኮ እና ናንቴስን፣ በስፔን ቫሌንሲያ እና አትሌቲኮ ማድሪድን፣ በጣሊያን ሮማ፣ ናፖሊ፣ ጁቬንቱስ፣ ኢንተርሚላንን እና ሌሎችንም በመዘዋወር በጠቅላላው 22 ቡድኖችን አሠልጥነዋል፡፡ ከረጅሙ የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ዘመናቸው የካበተ ልምድ እንደቀሰሙ ይነገርላቸዋል፡፡

በተለይ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ከሌስተር ሲቲ ጋር ታሪካዊውን ዋንጫ አንስተዋል፡፡ የግሪክን ብሔራዊ ቡድንምም አሠልጥነዋል፡፡ ክላውዲዮ ራኒየሪ የሚያሠለጥኑት የካግሊያሪ ቡድን የመጨረሻ ጨዋታውን ሲያደርግ አድናቂዎቻቸው “ዘላለማዊ ምሥጋና ለታላቅ ሰው” የሚል መልዕክት የተጻፈበት ‘ባነር’ በመያዝ ስማቸውን እየጠሩ ዘምረውላቸዋል፡፡ የተለያዩ ቡድኖች ተጫዋቾች፣ የሴሪኤው ዳኞች፣ በስታዲየም የታደሙት በርካታ ተመልካቾች ከወንበራቸው ተነስተው በከፍተኛ ጭብጨባ አድናቆታቸውን ለግሰዋቸዋል።

“የአሠልጣኝነት ሥራ በቃኝ ማለቴ ከባድ ቢኾንም ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አስባለሁ። ቦታውንም ለወጣት አሠልጣኞች መልቀቅ ተገቢ ነው” ብለዋል ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት አስነብቧል፡፡ የ72 ዓመቱ ጣሊያናዊው ክላውዲዮ ራኒየሪ ከ1973 እስከ 1986 ድረስ በአራት የተለያዩ ቡድኖች በተከላካይ መስመር በ366 ጨዋታዎች ተሰልፈው ተጫውተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here