ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሞገዶቹ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመኾን የጦና ንቦቹ ላለመውረድ ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።
ባሕር ዳር ከተማ በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታቸው ያስመዘገቡት ደካማ እንቅስቃሴ ውጤታቸውን ጎተታቸው እንጂ በቅርብ ሳምንታት በማሸነፍ ያስመዘገቡት ውጤት የመጀመሪያ የዋንጫ ተፎካካሪ በኾኑ ነበር፤ ግን አሁንም እረፈደ እንጅ አልመሸባቸውም።
አሁን ባሕር ዳር ከተማ በተለየ ጥንካሬ ላይ ይገኛል። ባለለፉት አስራ አንድ ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠማቸውም።
የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት የቡድኑ ዋና ጥንካሬ ነው። ከሽንፈት ከራቀባቸው አስራ አንድ ጨዋታዎች ውስጥ በስምንቱ መረቡን ሳያስደፍር ከመውጣቱም ባሻገር የተመዘገቡበት ግቦች ሦስት ብቻ ናቸው። ይህም አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጥሩ ቡድን መገንባታቸውን ያሳያል። በዛሬው ጨዋታ በባሕር ዳር ከተማ በኩል አንበሉ ያሬድ ባዬህ በጉዳት ምክንያት እንደማይሰለፍ ታውቋል። ጥሩው ዜና ደግሞ ቸርነት ጉግሳ እና ፍሬው ሰለሞን በዛሬው ጨዋታ ተሰላፊ ይኾናሉ።
በዛሬው ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ካሳኩ በሂሳባዊ ስሌት በሊጉ መቆየታቸው የሚያረጋግጡት ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው ዙር ያሳዩት ደካማ ጉዞ የመውረድ ስጋት ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል። በለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል። የቡድኑ የመከላከል ክፍተቶች ለውጤት ማጣቱም ዋና ምክኒያት ነው። በንግድ ባንክ አምስት ለባዶ የተሸነፉበት ጨዋታ ለዚህ ምስክር ነው።
ስለኾነም ዛሬ አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ የተከላካይ ክፍሉን ማሻሻል ቀዳሚ ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃሉ። በአንጻሩ የግብ ዕድል ፈጠራ ላይ የተዳከመው አጨዋወታቸውንም መፍትሔ የሚሻ ሌላው ጉዳይ ነው። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተዋል። ባሕርዳር ከተማ በሦስት አሸንፏል። ወላይታ ድቻ አንድ ጊዜ ረትቷል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ መለያየታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገጹ አስነብቧል።
በሌላ የዛሬ ጨዋታ ቀን 9 ሰዓት መቻል ከ ሻሸመኔ ከተማ ይጫወታሉ። በፕሪሚየር ሊጉ በ50 ነጥብ በሁለትኝነት የሚገኘው መቻል የዋንጫ ተፎካካሪ ነው። ተጋጣሚው ሻሸመኔ ላለመውረድ የሚያደረገው ጨዋታም በመኾኑ ትኩረት ስቧል። መቻል ከጨዋታ ጨዋታ የአጥቂው ክፍል ተጠናክሯል። የቡድኑ የአማካይ ክፍልም በማጥቃት ሂደቱ ላይ ያለው ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህም የፊት መስመሩን ጥንካሬ ከመጨመር አልፎ የግብ ምንጮቻቸውንም አስፍቶታል።
ቡድኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ደጋግሞ ለግብ ያልማል።ይህም ጥንካሬው ነው። ይህም ሆኖ አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የመከላከል አደረጃጀቱ ላይ ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል። በመቻል በኩል ግሩም ሐጎስ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም። በአስራ ሦስት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሻሸመኔ ከተማ በቅርብ ሳምንታት በብዙ ረገድ ተሻሽሎ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም ካሉበት ደረጃ ፈቀቅ ማለት አልቻለም።
ከዛሬ ው ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግን ከውጤትም በተጨማሪ ለቀጣይ ወሳኝ መርሐ ግብሮችም ፋይዳው ትልቅ ነው። ሻሸመኔ ከተማዎች በቅጣት ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ53 ነጥብ ይመረዋል። መቻል በ50 ነጥብ እንዲሁም ባሕር ዳር ከተማ በ44 ነጥብ ሦስተኛ መኾኑን ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ድረ ገጹ የተገኘው ማስረጃ ያሳያል። ወልቂጤ ከተማ በ16ነጥብ 14ኛ ነው። ሻሸመኔ ከተማ በ13 ነጥብ 15ሲኾን ሀምበሪቾ በስምንት ነጥብ መውረዱ ተረጋግጧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!