በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ለውጥ የሚያመጡ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

0
224

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሊጉ 26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ቀን ዘጠኝ ሰዓት ወልቂጤ ከተማ ከድሬ ዳዋ ከተማ ይጫወታሉ። የወራጅ ስጋት የተደቀነበት ወልቂጤ ከተማ ደካማ አቋም ላይ ከሚገኘው ድሬ ዳዋ ከተማ የሚጫወት ይኾናል። በ16 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ እጅግ አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። በሊጉ ባደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፏል። ውጤቱም የቡድኑን ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዬ ነው።

በወልቂጤ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ይመለሳል። በአንፃሩ በ34 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ድሬ ዳዋ ከተማ በከተማው በነበረው የሊጉ የጨዋታ ቆይታ ካሳየው መነቃቃት በኋላ ወደ ሀዋሳ ከመጣ ወዲህ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል።

ቡድኑ በሀዋሳ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፏል። በአንዱ ብቻ ነጥብ ተጋርቷል። ቡድኑ ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር በአንፃሩ ሰባት ግቦችን አስተናግዷል። በተለይም በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ መድን የደረሰበት የ5 ለ 0 ሽንፈት እጅግ አሳዛኝ ነበር።

ይህም ሽንፈት በ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን በ15ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በፋሲል ከነማ ከደረሰበት የ4 ለ 0 ሽንፈት በኋላ የታየ አስከፊ ውጤት ነው ተብሎ ተመዝግቧል። አሠልጣኝ ሽመልስ አበበ ከዚህ አስከፊ ሽንፈት ማግሥት በሥነ ልቦና ረገድ እየዋዥቀ የሚገኘውን ስብስብ አነቃቅቶ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ የማድረግ ወሳኝ የቤት ሥራ ይጠበቃቸዋል።

ድሬ ዳዋ የዛሬውን ጨዋታውን ካሸነፈ ደረጃው ወደ ስምንት ከፍ ይላል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ድሬ ዳዋ ሦስት ጊዜ አሸንፏል። ወልቂጤ ደግሞ ሁለት ጊዜ ባለድል ኾኗል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ምሽት 12 ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ መድን የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ጥንካሬውን አሳይቷል። በእነዚህ አምስት ጨዋታዎችም 13 ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ በአንፃሩ ያስተናገደው የግብ መጠን አንድ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው ዙር ጥያቄ ይነሳበት የነበረው የፊት መስመሩ በአጋማሽ በተጫዋች ዝውውር ወቅት ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ቡድኑ አጥቅቶ እንዲጫዎት አድርገዋል። ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ደግሞ በመጨረሻ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ድል ሲያደርግ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል፤ ይህም ነጥቡን 41 በማድረስ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ከረታ አራተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።

በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂውን ሰዒድ ሀብታሙን በቅጣት እንዲሁም ተከላካዩን አሕመድ ረሺድን በጉዳት በዛሬው ጨዋታ እንደማያገኙ ተረጋግጧል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 20 ጊዜ ተገናኝተዋል። አዳማ ሰባት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። መድን ሦስት ጨዋታ ሲያሸንፍ በ11 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ53 ነጥብ ይመራዋል። መቻል በ50 ነጥብ ይከተላል። ባሕር ዳር ከተማ ደግሞ በ44 ነጥብ ሦስተኛ ነው። ወልቂጤ14ኛ፣ ሻሸመኔ 15ኛ ሲኾኑ ሀምበሪቾ 16ኛ ደረጃን ይዛ መውረዱ ተረጋግጧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here