ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታዋን ዛሬ ከኬንያ ጋር ታደርጋለች። የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ናይሮቢ በሚገኘው ኡሊንዚ ስፖርት ኮምፕሌክስ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
8ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በዶሚኒካ ሪፐብሊክ አስተናጋጅነት በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ይደረጋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ በአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ ነው። በሦስተኛ ዙር የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከኬንያ ጋር ዛሬ ያደርጋል። ሁለቱ ሀገራት ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያካሄዱት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
ሉሲዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ጨዋታው በሚደረግበት ኡሉንዚ ስፖርት ኮምፕሌክስ ትናንት አድርገዋል። ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ራውዳ አሊ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ በሀገር ውስጥና በኬንያ ዝግጅት ማድረጉን ገልጻለች።
ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያለን እድል ማሸነፍ ብቻ በመሆኑ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንጥራለን ስትልም ተናግራለች። በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ብሔራዊ ቡድኑን ስታዲየም ተገኝተው እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርባለች። የኬንያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ማይልድሬድ ቼቼ በበኩሏ ጨዋታው ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን ካሸነፍን ለዓለም ዋንጫው ቅርብ መሆን እንችላለን ብላለች።
በጨዋታው የተቻለንን ሁሉ አድርገን ጥሩ ውጤት ለማግኘት እንሞክራለን፤ ግባችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ነው ስትልም ገልጻለች። ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በመጨረሻው ዙር ከብሩንዲ ጋር ትጫወታለች። አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሶስት ሀገራትን የማሳተፍ ኮታ ያላት ሲሆን 12 ሀገራት በውድድሩ ለመሳተፍ በሶስተኛው ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዓለም ዋንጫው 16 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን አዘጋጇ ዶሚኒካን ሪፐብሊክን ጨምሮ እንግሊዝ ፣ ፖላንድ፣ ስፔን፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ኒውዝላንድ፣ ጃፓን እና ሰሜን ኮሪያ እስከ አሁን ለዓለም ዋንጫው ያለፉ ሀገራት ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!