ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ቀን 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ፡፡ በሰላሣ ስምንት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማ ያለመሸነፍ ጉዞውን ለማስቀጠል እንዲሁም አሸንፎ ደረጃቸው ለማሻሻል እያለመ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታመናል።
ቡድኑ ከሽንፈት በራቀባቸው አራት ሳምንታት በሦስቱ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል፡፡ ይህም ቡድኑ በቅርቡ ያሳየውን መሻሻል ያሳያል፡፡ አዳማ ከተማ ይህን ጨዋታ ካሸነፈ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አለው፡፡ በተለይ ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዮሴፍ ታረቀኝ ለሙከራ ከሄደበት ዴንማርክ ተመልሶ የሚሰለፍ በመኾኑ ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። የዚህ ተጫዋች ተሳትፎ በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ለውጥ ማምጣቱ አያጠያይቅም።
በሰላሣ አንድ ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ባለፉት ስምንት ሳምንታት ያስመዘገበው ውጤት ከወራጅ ቀጣናው እንዲወጣ አስችሎታል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ የሚወጣ ከኾነም ደረጃው ይሻሻላል፡፡ እናም ጨዋታውን ወሳኝነት አለው፡፡ ሲዳማ ቡናዎች በዛሬው ጨዋታ በብዙ መለኪያዎች የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት የገነባውን እና ከመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ያላስደፈረውን ቡድን እንደመግጠማቸው የፊት መስመራቸውን አጠናክረው መግባት ግድ ይላቸዋል።
አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በአንፃራዊነት የተሻለ የሚያጠቃ ቡድን አዋቅረዋል፤ ዛሬው ከአዳማ ከተማ ጋር ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለሲዳማ ቡና ጊት ጋትኩት ከሁለት ጨዋታዎች ቅጣት ተመልሶ የሚሰለፍ ይኾናል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ25 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ሲዳማ ቡና ዘጠኝ አዳማ ከተማ ደግሞ ስድስት ጊዜያት ማሸነፍ ችሏል፡፡ በ10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ በወልቂጤ ከተማ መሸነፍ ከወራጅ ቀጣናው የመውጣት ወርቃማ ዕድል ያገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች አሸንፎ ሁለት ደረጃዎች ለማሻሻል ከሚያልመው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። በውድድር ዓመቱ ሁለት ድሎች ብቻ ያስመዘገበው ሻሸመኔ ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አግኝተዋል፡፡ ይህም የቡድኑን ደካማነት ያሳያል፡፡
ለሻሸመኔ ከተማ ወደ ሀገሩ ተጉዞ የነበረው ግብ ጠባቂው ኬን ሰይዲ ቡድኑን ተቀላቅሏል። በአንጻሩ አቤል ማሞን በጉዳት ምክንያት እንደማይሰለፍ ታውቋል ሲል ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል፡፡ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወላይታ ድቻን አሸንፈው ወደ ድል ተመልሰዋል፡፡ ቡናዎች ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ካገኙ ሁለት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል። ስለኾነም ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው በአራት አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ጨዋታ ያሸነፈ ሲሆን በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ፕሪምየር ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 የግብ ክፍያ እና በ50 ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡ መቻል በ11 የግብ ክፍያ እና በ47 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡ ባሕር ዳር ከተማ ደግሞ በስምንት የግብ ክፍያ እንዲሁም በ41 ነጥብ በሦስተኛነት ተቀምጧል፡፡ ፋሲል ከነማ ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!