ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ቀን 9 ሰዓት በተጀመረ ጨዋታ ሀምበሪቾ ከባሕር ዳር ከተማ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እየተጫወቱ ነው፡፡ ጨዋታውን በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጣና ሞገዶቹ 1 ለ 0 መርተው ጨርሰዋል። ባሕር ዳር ከተማ እስካሁን ባደረገው 24 ጨዋታዎች በ11 አሸንፏል፡፡ በስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል፡፡ በአምስቱ ደግሞ ተረትቷል፡፡
ባሕር ዳር ከተማ ከ24 ጨዋታዎች የተቆጠረበት የግብ ብዛት 19 ነው። ይህም የተከላካይ ክፍሉን ጥንካሬ ያመላክታል፡፡ በተለይ በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ግብ ተቆጥሮበታል ሲል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ቡድኑ በ24 ጨዋታዎች ስምንት ንጹህ ግብ እና 41 ነጥብ በመሰብሰብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የጣና ሞገዶቹ ላለፉት አሥር ሳምንታት ከሽንፈት መራቃቸው ጠንካራ ጎናቸው ነው። ይሁንና ቡድኑ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት ከአቻ ውጤቶች መላቀቅ ግድ ይለዋል።
በስምንት ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የተቀመጡት እና ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም የጣና ሞገዶቹን የገጠሙት ሀምበሪቾዎች በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን ለማለምለም በቀሩት ስድስት መርሐግብሮች ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን የሚጫዎቱ ይኾናል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!