ቫር/VAR/ ሊቋረጥ ይኾን?

0
219

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (ቫር) ይቀጥል ወይስ ይቋረጥ በሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ድምጽ ሊሰጡ ነው፡፡ ቫር በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሥራ ላይ የዋለው 2019-20 የውድድር ዘመን መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን እያደር ከቴክኖሎጂው ጋር የተያያዙ በርካታ አወዛጋቢ ክስተቶች ተስተውለዋል በሚል ቡድኖች ቅሬታ እያቀረቡበት ይገኛሉ፡፡

በ2023/ 2024 የውድድር ዘመን በተለይ የዎልቭስ ቡድን በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት ላይ እምነት እንዳጣበት ገልጾ ብዙ ያልተጠበቁ አሉታዊ ውጤቶች አስከትሎብናል ብሎል፡፡ በመኾኑም ቫር በቀጣዩ የውድድር ዘመን መተግበር እንደሌለበት በማመልከቻ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ ሊጉ በመተዳዳሪያ መመሪያው መሠረት የዎልቭስ ቡድን በውድድር ወቅት ያልተመቸውን ነገር ማቅረቡ መብቱ መኾኑን ጠቅሶ ሌሎች ቡድኖችም በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳብ እንዲሰጡበት ጠይቋል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ ቦርድ በበኩሉ በዎልቨስ ቡድን የቀረበውን ሀሳብ እንደሚቃወመው አስታውቋል፡፡ ይኸም ኾኖ በሚቀጥለው ወር ማለትም ሰኔ 6 ቀን 2024 በሚካሄደው የሊጉ ዓመታዊ አጠቃላይ ሥብሰባ 20 አባል ቡድኖች የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት ሥራው በቀጣዩ የውድድር ዘመን “ይሰረዝ” ወይስ “ይቀጥል” ለማለት ድምጽ እንዲሰጡበት ሊደረግ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሊጉ ዋና የእግር ኳስ ኃላፊ ቶኒ ስኮልስ ለስካይ ስፖርት በሰጡት ሀሳብ “ቫር በጣም ውጤታማ መሳሪያ ነው” ብለዋል፡፡ ለአብነት በሊጉ ስታትስቲክስ መሰረት በባለፈው ዓመት 83 በመቶ የቫር ውሳኔዎች ትክክል ነበሩ፡፡ በዚህ የውድድር ዘመን ቫር 96 በመቶ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ማስተላለፉንም ጠቁመዋል፡፡

ሊጉ የቫር ሥራውን በ2024-25 የውድድር ዘመን ለማስቀጠል ከ20 የፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ውስጥ የ14ቱን ድምጽ ማግኘት ይጠበቅበታል ነው የተባለው፡፡ ሊቨርፑል የቫርን መሰረዝ ከማይደግፉ ቡድኖች መካከል አንዱ መኾኑን ስካይ ስፖርት በዘገባው አስነብቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here