ዋንጫው የማንቸስተር ሲቲ ወይስ የአርሰናል?

0
383

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2023/24 የእንግሊዝ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ዋንጫውን ለመውሰድ ተፋጥጠዋል። አርሰናል 38ኛው የመጨረሻ ጨዋታ እየቀረው በ86 ነጥብ የሊጉ መሪ ነው። 36 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በ85 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ዛሬ ማንቸስተር ሲቲ በቶትንሀም ሜዳ ማሸነፍ ከቻለ መድፈኞችን በሁለት ነጥብ በልጦ መሪ ይኾናል። ዜጎቹ በጨዋታው አቻ ከወጡ ከመድፈኞቹ ጋር በነጥብ እኩል ይኾኑና በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ረግቶ ይቆያል ። የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ “ቶትንሐምን በሜዳው ለማሸነፍ እስካሁን ያልታዬ ለየት ያለ የጨዋታ ፍልስፍናን ይዘን እንቀርባለን” ብለዋል ።

አሠልጣኙ አክለውም ቡድናቸው “ማንቸስተር ሲቲ” በቶትንሐም ሜዳ ከዚህ ቀደም ተጫውቶ ማሸነፍ እንዳልቻለ ጠቁመዋል። “ዛሬ ለየት ያል ሥልት ይዘን በመጫወት ካላሸነፍን በቃ! ዋንጫው የአርሰናል ይኾናል” ብለዋል። የቶትንሐም አሠልጣኝ ፖስትኮግሎው “ደጋፊዎቻችን መቶ በመቶ ማንቸስተር ሲቲን እንድናሸንፍ ይፈልጋሉ። ወዲያ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ቡድናችን ከአቅም በታች ተጫውቶ እንዲሸነፍ ይሻሉ። ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ከስፖርት ሕግ ያፈነገጠ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች በጭራሽ ሀሳባቸውን አልቀበለውም፤ እኛ እንደ ሁልጊዜው ዛሬም ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን ለማሸነፍ ነው የምንጫዎተው” ብለዋል።

የአርሰናሉ አለቃ ሚኬል አርቴታ ከስካይ ስፖርትስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በእግር ኳስ ጨዋታ ሁል ጊዜ ዕድሎች አሉ። እኛም የማሸነፍ ዕድል አለን። በእውነት የቶትንሐምን የአሸናፊነት ውጤት እንፈልገዋለን፤ ለዚህም ነው ጨዋታውን በጉጉት እና በልዩ ስሜት ውስጥ ኾነን የምንከታተለው” በማለት ተናግረዋል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ተንታኝ ጋሪ ኔቪል ሁለቱም ቡድኖች በመጨረሻ ግጥሚያዎች እንደሚያሸንፉ ያምናሉ። ስለኾነም ዛሬ በቶትንሐም ሆትስፐር ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ የሊጉ ዋንጫ ወደየት ቡድን እንደሚሄድ ይጠቁማል ብሏል። አርሰናል 38ኛ እና የማሳረጊያ ጨዋታውን የፊታችን እሑድ ከኤቨርተን ጋር ያደርጋል። ማንቸስተር ሲቲም 38ኛ ጨዋታውን በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት ከዌስትሐም ዩናይትድ ጋር ይጫወታል። ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ይካሄዳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here