ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ መድን ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫዎታሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት፤ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅ የሚያስችላቸውን ነጥብ ለማስመዝገብ ይፋለማሉ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ23 ጨዋታዎች 11ዱን አሸንፎ፣ በስድስቱ አቻ ተለያይቶ፣ በስድስቱ ደግሞ ተሸንፎ 39 ነጥብ በመሠብስብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እና ቡድኑ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግዶ ነው ዛሬ ወደ ሜዳ የሚገባው፡፡ ቡድኑ በተከታታይ ባካሄዳቸው አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ ማሳካት የቻለው ሁለቱን ብቻ ነው፤ ይህንን ተከትሎም ከሰባት ሳምንታት በፊት ሊጉን በመምራት ላይ የነበረው ቡድኑ አሁን ከመሪው ንግድ ባንክ በሰባት ነጥብ ለመራቅ ተገዷል።
በዛሬው ጨዋታም በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ያለውን እድል ጨርሶ እንዳያጣ ከማሸነፍ ውጪ ኾነ ውጤት ትርፋማ አያደርገውም። ፈረሰኞቹ ጨዋታውን ካሸነፉ ባሕር ዳር ከተማ ትናንት ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ መለያየቱን ተከትሎ የባሕር ዳርን የሦስተኛነት ደረጃ የሚረከብ ይኾናል፡፡በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉና ሞሰስ አዶ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።
ኢትዮጵያ መድንም በሊጉ 23 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በአምስት ጨዋታዎች አሸንፎ፣ በ10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በስምንት ተሸንፎ በስድስት አሸንፎ 25 ነጥብ ብቻ በመያዝ በወራጅ ቀጣናው በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ደካማ የተከላካይ ክፍሉን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በማስተካከሉ አንድ ግብ ብቻ ተቆጥሮበታል፡፡ በመኾኑም የቡድኑ የተከላካይ መስመር ለፈረሰኞቹ ይፈትናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመድን የፊት መስመርም ከጨዋታ ጨዋታ በመሻሻሉ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ይህ ሆኖም ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ የግብ ዕድሎችን ማባከኑ የአጥቂው ክፍል ወጥ አቋም እንደሌለው ያሳያል። እናም በዛሬው ጨዋታ ዋጋ እንዳያስከፍለለው አጥቂዎች ተናበው መጫዎት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 26 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 19 ጊዜ አሸንፏል፡፡ መድን በአንጻሩ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶታል፡፡ በአምስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚገናኙበት ጨዋታም ይጠበቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!