ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲን ለዋንጫው አፋጥጦ ቀጥሏል። አርሰናል ሊጉን ከሲቲ በአንድ ነጥብ በልጦ እየመራ ነው። ነገር ግን የጋርዲዮላው ቡድን ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ እጁ ላይ አለ። ሁለቱ ክለቦች በቀጣይ የሚያስመዘግቡት ውጤትም በጉጉት ይጠበቃል።
ለዋንጫ ከሚደረገው ፉክክር ተጠባቂነት ጎን ለጎን ከተጫዋቾች ውስጥ የዓመቱ የፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ማን ይኾናል የሚለውም የብዙዎች ትኩረት ነው። በቢቢሲ መረጃ መሰረት የፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ተጫዋች ለመባልም ስምንት እጩዎች ቀርበዋል። የአርሰናሎቹ ማርቲን ኦዲጋርድ እና ደክላን ራይስ፣ ፊል ፎደን እና ሀላንድ ከማንቸስተር ሲቲ፣ የኒውካስትሉ ኤሌክሳንድር ኢሳቅ፣ ኦሌ ዋትኪንስ ከአስቶን ቪላ፣ ኮል ፓልመር ከቼልሲ እና የሊቨርፑሉ ቨርጅል ቫንዳይክ እጩዎች ናቸው።
በእጩዎች ዝርዝር ውስጥ የማንቸስተር ሲቲው ሮድሪጎ፣ የኒውካስትሉ አንቶኒ ጎርደን እና የበርንማውዙ ዶሚንክ ሶላንኬ አለመካተታቸው አስገራሚ ነው ብሏል ቢቢሲ በዘገባው። በተመሳሳይ የዓመቱ ምርጥ አሠልጣኝ ለመባል ማይከል አርቴታ፣ ፔፕ ጋርዲዮላ፣ የርገን ክሎፕ፣ ኡናይ ኢምሬ እና የበርንማውዙ አሠልጣኝ አንዶኒ ራኦላ እጬ ኾነዋል።
የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች እጩዎችም ታውቀዋል። ፎደን፣ ሀላንድ፣ ኢሳቅ እና ፓልመር ከአዋቂዎች በተጨማሪ በዚህ ዘርፍም እጬ ኾነው ቀርበዋል። ቡካዮ ሳካ፣ ዊልያም ሳሊባ፣ ኮቢ ማይኑ እና ደስትኒ ኦዲጊ ደግሞ ቀሪዎቹ እጬዎች ናቸው። ባለፈው ዓመት በአዋቂዎችም ኾነ በወጣቶች ዘርፍ የኮከብነት ክብር ባለቤቱ ሀላንድ እንደነበር ይታወሳል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!