ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዛሬ መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ ከባሕር ዳር ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ቀን 9 ሰዓት ላይ ይጫዎታሉ፡፡ ፋሲል ከነማ በሊጉ 23 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በዘጠኝ ጨዋታዎቸ አሸንፎ፣ በዘጠኝ አቻ ተለያይቷል፡፡ በአምስት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል፡፡ ቡድኑ ዘጠኝ ንጹህ የግብ ክፍያ በመያዝ በ36 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ፋሲል ከነማዎች በዚህ የውድድር ዘመን በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን ለዋናው ቡድን እያበቁ ይገኛሉ፡፡ ይህም ይበል እያሰኛቸው ይገኛል፡፡ ለአብነት ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ወጣቱ ጃቢር ሙሉ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ነበር። ተጫዋቹ ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን ሲረታ ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለሰች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችሏልና። ወጣቱ ዮሐንስ ደርሶም ለፋሲል ሌላኛው የዘንድሮ የውድድር ዘመን ስኬት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቡድኑ ካለው ልምድ እና ከያዛቸው ወሳኝ ተጫዋቾች አንጻር በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ ይሁን እና በቀጣይ ቀሪ የሊጉ መርሐ ግብሮች የተሻለ ሥፍራን ይዞ ለማጠናቀቅ ጥረት ስለሚያደርግ ዛሬ ባሕር ዳር ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው። በዛሬው ጨዋታ ድል የሚቀናቸው ከኾነም ረጃቸውን ማሻሻል ይችላሉ።
ዐጼዎቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ አፍቅሮተ ሰለሞን፣ ይሁን እንዳሻው እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በጉዳት ምክንያት እንደማያሰልፍ ተረጋግጧል፡፡ የጌታነህ ከበደ መግባትም አጠራጣሪ ኾኗል፡፡ ባሕር ዳር ከተማ ከ23 ጨዋታዎች 11ዱን አሸንፎ፣ በሰባቱ አቻ ተለያይቶ፣ በአምስቱ ተሸንፎ፣ በስምንት የግብ ክፍያ 40 ነጥብ በመሠብሠብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ቡድኑ በተሻለ የውጤታማነት ጉዞ ላይ ቢገኝም ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥርበት ተሰግቷል፡፡ ያሬድ ባየህ እና ሙጂብ ቃሲምን በጉዳት ያጣው ባሕር ዳር ከተማ በ23ኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የኾነውን ቸርነት ጉግሳንም በጉዳት ምክንያት መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ቸርነት ለዛሬው ጨዋታ ብቁ መኾኑም
አልተረጋገጠም። የጣና ሞገዶቹ ጨዋታውን ካሸነፉ ይበልጥ መደመሪዎች ይቀርባሉ። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ለዘጠኝ ያህል ጊዜያት ተገናኝተዋል፤ ፋሲል ሁለት ጊዜ እንዲሁም ባሕር ዳር አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሸር ካንፓኒ መረጃ ምሽት 12 ሰዓት በ33 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በ37 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ የያዘውን አዳማ ከተማን ያስተናግዳል፡፡
አዳማ ካሸነፈ ለጊዜውም ቢኾን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃን ሲረከብ በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ ከረታ ደረጃውን በአንድ የሚያሻሽል ይኾናል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ47 ነጥብ ሲመራው መቻል በ44 ነጥብ በሁለተኛነት ይከተላል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!