ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2027 የሚደረገውን 10ኛውን የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት በአንድ በኩል ብራዚል በሌላ ወገን ደግሞ ቤልጀየም፣ ኔዘርላንድስ እና ጀርመን በጋራ ማዘጋጀት እንደሚሹ ለፊፋ አመልክተዋል፡፡ ፊፋም የእያንዳንዱን አመልካች ሀገር መሠረተ ልማት እና ደኅንነት ሰፊ ምልከታ አድርጓል፡፡ ስለኾነም የደረሰበትን ድምዳሜ ግንቦት 17/2024 በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ በሚያደርገው 74ኛ ስብሰባው ያቀርባል ተብሎ ተጠብቋል፡፡ በዕለቱም 211 የፊፋ አባል ሀገራት 10ኛውን የሴቶች የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ለመምረጥ ድምጽ ይሰጣሉ ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ብራዚል እንደ አውሮፓ አቆጣጠር የ1950 እና 2014 የወንዶች የዓለም ዋንጫን እንዲሁም በ2016 የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ማዘጋጀቷ ይታዎሳል፡፡ በተለይ ለ2016 ኦሊምፒክ ታስበው የተገነቡ ወይም እድሳት የተደረገላቸው ስታዲየሞች የ2027ቱን የሴቶችን ዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ያስችላታልም እየተባለ ይገኛል፡፡
አንድ ስማቸው እና ሀገራቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፊፋ ባልደረባ እንዳሉት የፊፋ የቴክኒክ ገምጋሚ ቡድን ለብራዚል ከአምስቱ በአማካይ 4 ነጥብ ተሰጥቷታል ነው ያሉት፤ በአንጻሩ የአውሮፓ ሀገራቱ 3 ነጥብ 7 ማግነኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ስለኾነም ብራዚል የሴቶችን ዓለም ዋንጫ እንድታስተናግድ ዕድሉ እንዲሰጣት የሚሹ ሀገራት በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡
የብራዚል ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ የሴቶችን ዓለም ዋንጫ በደቡብ አሜሪካ አሕጉር ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ይኾናል ነው የተባለው። አሜሪካ እና ሜክሲኮ የ2027ቱ የሴቶች የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት በጋራ ያቀረቡትን ጥያቄ ማንሳታቸውን ኤፒ ኒውስ በዘገባው አስታዉሷል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!