የግዮን ንግስቶች-ባሕር ዳር ከነማ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አለፈ።

0
234

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሴቶች እግር ኳስ ቡድን (የግዮን ንግስቶች) ወደ ኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በማለፉ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የቡድኑን ማለፍ አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ባሕር ዳር ከተማን በተለያዩ ጉልህ ድሎች በማጀብ የከተማችን ደረጃ እንደወትሮው ሁሉ እንደደመቀ እንዲቀጥል ከተማ አሥተዳደሩ በትጋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

አሁን ላይ ከተማችን በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ስፖርታዊ የውድድር መድረኮች በስድስት ቡድኖች ተወክሎ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ቡድኖችም በወንዶች እግር ኳስ፣ በሴቶች እግር ኳስ፣ በታዳጊዎች እግር ኳስ፣ በወንዶች መረብ ኳስ፣ በሴቶች ቅርጫት ኳስ እና በወንዶች እጅ ኳስ ሲሆን አሁን ላይ የግዮን ንግስቶች ከነበሩበት አንደኛ ዲቪዚዮን ወደ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ማደጋቸው ደግሞ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

በግዮን ንግስቶች የተገኘው ድል የባሕር ዳር ከተማን በስፖርት ቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ታዳጊ ክለቦች አበረታችና ከተማዋን በርካታ የእግር ኳስ ኮኮቦች እንዲወጡ ፋና ወጊ ተደርጎ የሚቆጠር እንደሆነም አንስተዋል፡፡ የግዮን ንግስቶች ባስመዘገቡት ድል የከተማ አሥተዳደሩ በስፖርታዊ ተሳትፎው የሚያደርገው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የግዮን ንግሥቶች ያስመዘገቡት ውጤት በድል ታጅቦ እንዲቀጥል ከተማ አሥተዳድሩ ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የሴቶች እግርኳስ ቡድን (የግዮን ንግስቶች) ከነበሩበት አንደኛ ዲቪዚዮን ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በመቀላቀላቸው ለከተማችን ሕዝብ፣ ለስፖርት ቤተሰቡና ደጋፊዎቻችን እንዲሁም ይህ ውጤት እንዲመዘገብ በትጋት ለሠሩ የባሕር ዳር ከተማ ስፖርት ክለብ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ለከተማ አሥተዳድራችን በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች፣ የባሕር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊ ማኅበር አመራሮችና ደጋፊዎች፣ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስተላልፈዋል።

መረጃው የባሕር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ነው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here