ቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ጨዋታውን ከሃዋሳ ከተማ ጋር ያደርጋል፡፡

0
277

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችለውን ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምሽት 12 ሰዓት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደርጋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መረጃ ፈረሰኞቹ በ22 ሳምንታት የጨዋታ መርሐ ግብር ውስጥ ካከናዎኑት 22 ጨዋታዎች በ11 አሸንፈዋል፡፡ በስድስቱ አቻ ተለያይተው እና በአምስቱ ተሸንፈው 15 ንጹህ የግብ ከፍያ በመያዝ በ39 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

ቡድኑ ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት ያለው በመኾኑ በ22 ጨዋታዎች 34 ግብ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል፡፡ይህም ኾኖ ባለፉት አራት ጨዋታዎች የአጥቂው ክፍል ተቀዘቅዞ ታይቷል፡፡ የአሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድን በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ፍጻሜ በመቁጠር መቅረብ ይኖርበታል፡፡

የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በጥሩ አቋም ላይ መገኘቱ ለዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ተስፋ ሰጪ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ18 ንጹህ የግብ ክፍያ እና በ43 ነጥብ እየመራው ይገኛል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከመሪው ቡድን ጋር የሚኖረው የነጥብ ልዩነት አንድ ብቻ ይኾናል፤ ለዚህም ነው ጨዋታው ወሳኝ ነው የተባለው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሞሰስ አዶን በዛሬው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ማሰለፍ አይችልም፡፡ ሃዋሳ ከተማ በ22 ጨዋታ ስምንቱን አሸንፎ፣ በአምስቱ አቻ ተለያይቶ፣ በዘጠኝ ጨዋታ ተረትቶ፣ በሁለት የግብ ዕዳ እና በ29 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ አሁን ያለበት ደረጃ ለአደጋ የሚያጋልጠው ባይኾንም የውድድር ዓመቱን በጥሩ ደረጃ ለማጠናቀቅ ከሚታይበት የወጥነት ችግር መላቀቅ አለበት። ያም ኾኖ ቡድኑ ግብ ማስቆጠር የማይሳነው የፊት መስመር ቢኖረውም ደካማውን የመከላከል አደረጃጀት ከወዲሁ የማስተካከል ሥራ ይጠብቀዋል፡፡

በሃዋሳ ከተማ በኩል በቅጣትም ኾነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ሁለቱ ቡድኖች 48 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 ጨዋታ አሸንፏል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሰባት ጊዜ ድል ነስቷል፡፡ በ12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። በሌላ በኩል ቀን 9 ሰዓት ላይ በሊጉ 40 ነጥብ እና ሰባት የግብ ክፍያ በመያዝ በሁለተኛነት የተቀመጠው መቻል ከወልቂጤ ከተማ ይጫወታል፡፡

ወልቂጤ ከተማ ላለመውረድ እንደመጫወቱ መቻልን ይፈትነዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በጨዋታው መቻል የሚያሸንፍ ከኾነ ፈረሰኞቹ ቢያሸንፉም ሦስተኛ ደረጃን እንደያዙ የሚቆዩ ይኾናሉ፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here