ባሕር ዳር ከተማ የዋንጫ ተፎካሪ ለመኾን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል፡፡

0
266

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ37 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ የሚገኙት ባሕር ዳር ከተማዎች በሊጉ ባደረጓቸው የመጨረሻ ስምንት ጨዋታዎች አምስቱን ረትተዋል፡፡ በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብን በመጋራት ጥሩ እምርታ ላይ ይገኛሉ። በአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት የጣና ሞገዶቹ ለስምንት ጨዋታዎች የዘለቀውን ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ለማስቀጠል ዛሬ ድሬዳዋን ይገጥማሉ። ለዚህም እስካሁን በሊጉ 11 ግብ ባስቆጠረላቸው ቸርነት ጉግሳ ላይ እምነታቸውን የሚጥሉ ይኾናል። በባሕር ዳር ከተማ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ሙጅብ ቃሲም ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው፡፡

በአንጻሩ በ33 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ በንጽጽር የተሻለ የውጤታማነት ጉዞ ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ሊጉ በድሬዳዋ በነበረው ቆይታ በሀዋሳ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጭ እጅግ አስደናቂ ጊዜን ማሳለፍ ችለዋል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርልስ ሙሴጌ መጎዳት በኃላ በቡድኑ የፊት መስመር ተደጋጋሚ የመሰለፍ ዕድልን እያገኘ የሚገኘው ካርሎስ ዳምጠው ለቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ መኾኑን እያሳየ ይገኛል።

ካርሎስ አብዛኛውን ጨዋታ ከተጠባባቂ ወንበር ላይ እየተነሳ የተጫወተ ቢኾንም ከሰሞኑ ግን በቋሚነት የመሰለፍ እድል አግኝቷል፡፡ ተጫዋቹ በድምሩ አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ድሬዎች ከካርሎስ አብዝተው ይጠብቃሉ። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ሦስት ተጫዋቾች ከጉዳት ተመልሰዋል፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት ተመስገን ደረሰ እና ዓብዱልፈታህ ዓሊ እንዲሁም የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቻርለስ ሙሴጌ ከጉዳት መልስ ቡድናቸውን የሚያገለግሉ ተጫዋቾች ሲኾኑ ያሲን ጀማል ግን አሁንም ጉዳት ላይ ነው።

ሶከር ኢትዮጵያ እንደዘገበው ሁለቱ ቡድኖች በድምሩ በሊጉ በዘጠኝ አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል፡፡ በሦስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተለያይተዋል፡፡ ባሕር ዳር ከተማዎች በአምስት ጨዋታዎች ባለድል ናቸው፡፡ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በአንድ ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ በጨዋታዎቹ ባሕር ዳሮች አስራ ስምንት እንዲሁም ድሬዎች ደግሞ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።ጨዋታው ምሽት 12 ሰዓት ይጀምራል። በሌላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ቀን 9 ሰዓት አዳማ ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ የሚጫወቱ ይኾናል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here