ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ብዙዎችን ተፎካካሪዎች ከመንገድ በመተው አሁን አራት ቡድኖችን አስቀርቷል። አነዚህ ቡድኖች ለፍጻሜ ለመድረስ የመጀመሪያ ዙር ፈተናቸውን ዛሬ እና ነገ ያካሂዳሉ። የሞት ሽረቱ የመጨረሻ ትግል ደግሞ ሳምንት ይቀጥላል።
ዛሬ ትልቅ ግምት የተሰጠው እና በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ጨዋታ በባየርሙኒክ እና ሪያልማድሪድ መካከል ይደረጋል። ባየርሙኒክ አርሰናልን፣ ሪያልማድሪድ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሱት።
የዛሬው ጨዋታ በባየርሙኒኩ አሊያንዝ አሪና ሜዳ ይካሄዳል። የሙኒኩ አሠልጣኝ ቶማስ ቱሄል “ከሪያልማድሪድ ጋር ስትጫወት በሻምፒዮንስ ሊጉ ያለውን የበላይነት መጋፈጥ ያስፈልጋል፣ በግለሰብ ምርጥ ተጫዋቾች አሏቸው፣ በውድድሩ ያላቸው ልምድም ሌላ ፈተና ነው” የሚል ሃሳብ አንስተዋል።
አሠልጣኙ በተለይ እንግሊዛዊውን ኮከብ ጁዲ ቤልንግሃምን አድንቀዋል። በቦንደስሊጋው ድንቅ ነበር፤ በማድሪድ ቤትም አስገራሚ ብቃት እያሳየ ነው ብለዋል። በዛሬው ጨዋታም ተጫዋቹን ለማቆም የተለየ መላ እናበጃለን የሚል ሃሳብ መስጠታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።
የማድሪዱ አቻቸው ካርሎ አንቾሎቲ ደግሞ በራስ መተማናችን ከፍተኛ ነው፣ ሪያልማድሪድ በዚህ ውድድር ትልቅ ታሪክ ያለው እና የትልልቅ ተጫዋቾች ባለቤት ነው። እዚህ የደረስነው በጠንካራ ሥራ ነው ብለዋል።
በጨዋታው ሁለቱ እንግሊዛዉያን ሀሪኬን እና ጁዲ ቤልንግሃም ተጠባቂ ናቸው። ዋንጫ ፍለጋ ባየርሙኒክን የመረጠው ሀሪ ኬን እድለቢስ የሚል መገለጫውን ፉርሽ ለማድረግ ብቸኛ የዋንጫ እድሉ ሻምፒዮንስ ሊጉ ነው። አጥቂው በሙኒክ መለያ በግሉ ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ ነው። አስካሁን 42 ግቦችን አስቆጥሯል። በሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ ሰባት አስቆጥሮ ሦስት የጎል ኳሶችን ሰጥቷል።
ሌላው እንግላዛዊ ቤሊንግሃም ከማድሪድ ጋር ከፍ ብሎ እየበረረ ነው። ለክለቡ 21 ግብ አስቆጥሯል፣ አራቱ በሻምፒዮንስ ሊጉ ነው ያስቆጠራቸው። ከክለቡ ጋር በላሊጋ ዋንጫው ለመድመቅም ጫፍ ደርሷል።
በባለሜዳው ባየርሙኒክ በኩል ባለመሰለፋቸው ቡድኑን ሊያጎሉ የሚችሉ ተጫዋቾች በጉዳት ላይሰለፉ ይችላሉ። በዚህ ዝርዝር ውስጥም ኪንግስሊ ኮማን፣ ማቲያስ ዲሊት፣ ሊሮይ ሳኔ እና ጀማል ሙሴላን ጨምሮ ሌሎች ይገኙበታል።
ባየርሙኒክ እና ሪያልማድሪድ በቅርብ በተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስቱ በስፔኑ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቀዋል። የጀርመኑ ክለብ የአንዱን አሸናፊነት ወስዷል፣ ቀሪው አቻ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው።
የሁለቱ ኅያላን ፍጻሜ ላይ ራስን ለማግኘት የሚደረግ ትንቅንቅ ዛሬ በጀርመኗ ሙኒክ ተጀምሮ ሳምንት በስፔኗ ማድሪድ ይጠናቀቃል።
ጨዋታው ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ይደረጋል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!