ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ግብጻዊው የሊቨርፑል የፊት መስመር ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህ በአዲሱ አለቃው የአርኔ ስቶል ቡድን ቁልፍ አባል በመኾን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን እየተዘጋጀ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። ሊቨርፑል ከዌስትሃም ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ ሞሐመድ ሳላህ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ከመውጣቱ በፊት ከአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጋር ሲጨቃጨቅ ታይቷል። ይኽም በተጫዋቹ የመርሲሳይድ ቆይታ ላይ ጥርጣሬዎችን አሳድሯል።
የ31 ዓመቱ ሳላህ ከጨዋታው በኋላ በጉዳዩ ላይ ለጋዜጠኞች የተብራራ ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥቦ “ብናገር እሳት ሊነሳ ይችላል” ማለቱ ብቻ ተዘግቧል፡፡ ተጫዋቹ ከአሠልጣኝ የርገን ክሎፕ ጋር እላፊ የመነጋገሩ ምልክት በክረምቱ የተጫዋቾች የዝወውር ወቅት ሊቨርፑልን ሊለቅ ስላሰበ እንደኾነ ሲናፈስ ቆይቷል፡፡
በዚህ ላይ የሳዑዲ አረቢያ ክለቦች ግብጻዊውን ተጫዋች ለማስፈረም 70 ሚሊዮን ፓውንድ አቅርበዋል መባሉ ይታዎሳል፡፡ ዘ አትሌቲክስ እንደዘገበው ሳላህ በክሎፕ ላይ ያለውን ንዴት ተከትሎ ቡድኑን ለመልቀቅ አላሰበም ተብሏል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!