ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ብራዚላዊው ተከላካይ ከአራት ዓመታት የቼልሲ ቆይታ በኋላ 2023/24 የውድድር ዘመን መጨረሻ ከቼልሲ ጋር ይለያያል። ቲያጎ ሲልቫ በ2020 ከፓሪስ ሴንት ዠርሜ በነፃ ዝውውር ቼልሲን መቀላቀሉ ይታወሳል። ለሰማያዊዎቹ 151 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ቼልሲ በ2020-21 የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግን፣ የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫን እና የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫን ሲነሳ የተጫዋቹ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በዳይናሞ ሞስኮ፣በፍሉሚኔንስ፣በኤሲ ሚላን፣በፓሪስ ሴንት ዥርሜን እና በሌሎችም ቡድኖች መጫወት ችሏል።
ለብራዚል ብሔራዊ ቡድኑ በ121 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሰባት ብሔራዊ ግብ በስሙ አስመዝግቧል፡፡ የ39 አመቱ ሲልቫ ለቡድኑ ለቼልሲ ያለው ፍቅር “በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነው” ብሏል።አያይዞም “ለእኔ በቼልሲ መጫወት ትልቅ ትርጉም አለው። ከእኔ ባለፈ ልጆቼ ለቼልሲ ይጫወታሉ ብየ አስባለሁ” ነው ያለው፡፡
ተጫዋቹ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለቼልሲ በሁሉም ውድድሮች 34 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በፕሪሜየር ሊጉ ደግሞ በ25 ጨዋታዎች መሰለፍ ችሏል ሲል ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!