የተቀዛቀዘው ቮሊ ቦል/መረብ ኳስ/!

0
237

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሰንደቁ ወለላው ውልደት እና እድገታቸው በባሕር ዳር ከተማ ነው። በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ተዘዋውረው መንግሥታዊ በኾኑ እና ባልኾኑ መሥሪያ ቤቶች ሠርተዋል፤ በኮሌጆችም አስተምረዋል። ከ1970ዎቹ እስከ 1990ዎቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን እና መምህራንን በቮሊ ቦል ጨዋታ የሚያሳልፉት የአብሮነት እና የአንድነት ስሜት የተለየ እንደነበር ያስታውሳሉ።

እሳቸውም ተማሪ በነበሩበት ወቅት በባሕር ዳር ከተማ 12ኛ ክፍል እስኪ ጨርሱ ድረስ ቮሊ ቦል ይጫወቱ እንደነበር ያወሳሉ። በዚህም ብዙ አትርፊያለሁ ይላሉ። በትምህርት ቤት የተጀመረው የቮሊ ቦል ፍቅር አድጎ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ባሕር ዳር ከነማ፣ለግሥላ፣ ለሕንጻ ኮንስትራክሽን እና ለምዕራብ ዕዝ የአንደኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች እንዲጫወቱ አግዟቸዋል።

“በእኛ ጊዜ በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቅጥር ግቢ መረብ ኳስ ይዘወተር ነበር፣ በከተማ ደረጃም ውድድሮች ዓመቱን ሙሉ ይካሄዱ ነበር። ይህም ለእርስ በእርስ ግንኙነት ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩን ያስታውሳሉ። የእግር ኳስ ቡድን ያለው አንድ ተቋም የቮሊ ቦል ቡድን የመያዝ ግዴታም ይጣልበት ነበር። በወቅቱ ስፖርት ኮሚሽን ይባል የነበረው መሥሪያ ቤትም ይህ ዓይነቱን አሠራር መተግበሩ የቮሊ ቦል ጨዋታ ለዓመታት እንደሞቀ እና እንደ ተወደደ እንዲዘልቅ አድርጎት ቆይቷል ባይ ናቸው።

“ዛሬ ግን ዘርፉን አንዳንዶቹ የተቋማት መሪዎች ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሲጠቀሙበት እናስተውላለን” የሚሉት አቶ ሰንደቁ ፤ መሪዎቹ ከሥልጣን ሲለቁ ወይም ሲነሱ በእነሱ ይኹንታ የተመሰረተው ቡድን ሲፈርስ እያዬን ነው። በዚህም ስፖርቱ እንዲያድግ የአንዳንድ መሪዎች የተንሸዋረረ ምልከታ መስተካከል ይገባዋል ነው ያሉት።

“ቮሊ ቦል እንደ እግር ኳስ ለልምምድም ይኹን ለውድድር ሰፊ ሜዳ አይጠይቅም። በመኾኑም ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ሳይቀር ቡድን ቢያቋቁሙ እየተቀዛቀዘ ያለውን የቮሊ ቦል ጨዋታ በሰፊው ማነቃቃት ይቻላል”በማለት ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።

ሌላው አስተያዬት ሰጪ መዝገቡ ልዑልነህ ይባላሉ። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በግምጃ ቤት ወረዳ የስፖርት መምህር እና የቮሊ ቦል ተጫዋች ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የቮሊ ቦል ጨዋታ ትኩረት ተነፍጎታል። እሳቸው በሚኖሩበት ብሔረሰብ አሥተደደር ለመረብ ኳስ ስፖርተኞች ደመወዝ እየቆረጠ፣ አስፈላጊውን ቁሳቁስ እያቀረበ ፣ውድድሮችን እያመቻቸ እና ተተኪዎችን እየተቀበለ ለስፖርቱ የሚተጋ ተቋም እንዳላጋጠማቸው መስክረዋል።

እየጠፋ ያለውን የቮሊ ቦል ስፖርት መልሶ እንዲያንሰራራ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ውድድሮችን ማድረግ አለባቸው። ተቋማትም የመረብ ኳስ ቡድንን ቢይዙ ጊዜያዊ መፍትሔ ይኾናል ባይናቸው መምህር መዝገቡ ። አሚናት ሽኩር ደግሞ የ13 ዓመት ታዳጊ እያሉ በሚኖሩበት ቀበሌ በታዳጊዎች ቡድን ቮሊ ቦል መጫወት መጀመራቸውን ነው የነገሩን። አሚናት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በመኾናቸው አባታቸው ቁምጣ ለብሰው ሜዳ ላይ እንዲጫወቱ አይፈቅዱም ነበር።

በአንጻሩ ወላጅ እናታቸው “ልጄ የምትፍልገውን ትኾን ልንፈቅድላት ይገባል”በማለት ባለቤታቸውን ተቃውመው ከልጃቸው ጎን ቆሙ።ልጃቸው ጨዋታ ሲኖራቸው ሜዳ በመሄድም ያበረታቷቸው እንደነበር አሚናት ዛሬ ላይ በበጎ ጎኑ ያስታውሱታል። በልጅነት አእምሮ የተጠነሰሰውን የቮሊ ቦል ፍቅር አሚናት እውን ለማድረግ ለፍተዋል፤ ጥረዋል፤ የአባታቸውን ተቃርኗዊ ሐሳብ አሸንፈውም ድንቅ ችሎታቸውን በማሳየት ራሳቸውን ፈልገው እንዳገኙ ተናግረዋል።

“ከትምህርቴ ጎን ለጎን ቀሪ ጊዜዬን የማሳልፈው ቮሊ ቦል በመጫወት ነበር። በወቅቱ በማሳየው ጥሩ ብቃትም በአብዮት ፍሬ ቡድን ታቅፌ አምስት ቁጥር መለያ ለብሼ በመጫወት የክለብ ጉዞዬን ጀመርኩ ሲሉ ያስታውሳሉ። በወቅቱ ለቮሊ ቦል ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱት አሚናት ከሀገር ውስጥ ባለፈ በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ግብጽ እና ፒዮንግ ያንግ ድረስ በመሄድ ተጫውተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቮሊ ቦል ቡድን በአፍሪካ ደረጃ ጥሩ ስም ነበረው፤ በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ይፈሩናልም፣ ያከብሩን ነበር ይላሉ። አሚናት ዛሬ ግን ዘርፉ ከመዘንጋቱ አኳያ ወጣቱ “መረብ/ቮሊ ቦል/ እና እጅ ኳስ “ከማይለይበት ደረጃ ተደርሷል በማለት የቮሊ ቦል ጨዋታ እየተቀዛቀዘ መኾኑን መናገራቸውን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።

የአማራ ክልል ቮሊ ቦል ⎡መረብ ኳስ⎭ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታነህ መንግሥቴ መረብ ኳስ ተዳክሟል ለማለት ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር በጥናት በመለየት ማነጻጸር ይጠይቃል ብለዋል ። ነገር ግን ቮሊ ቦል በተለያዩ ምክንያቶች መቀዛቀዙን መናገር ይቻላል” ነው ያሉት።

መፍትሄውስ ምንድን ነው?” ላልናቸው ጥያቄ የክልሉ ሰላም ሲሠፍን የምንነጋገርበት ጉዳይ ቢኾን እመርጣለሁ” በማለት የተብራራ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይኾኑ ቀርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here