ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከሰኔ 14 እስከ ሐምሌ 14/2024 የሚካሄደው እና 24 ሀገራትን በሚያሳትፈው በዚህ ውድድር 51 የጨዋታ መርሐ ግብሮች ይስተናገዱበታል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የዳኞች ኮሚቴ ጨዋታውን የሚመሩ 19 ዳኞችን ከአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት መምረጡን ይፋ አድርጓል፡፡
የማኅበሩ የዳኞች ኮሚቴ ዳይሬክተር ሮቤርቶ ሮዜቲ “የአውሮፓ የእግር ኳስ ዋንጫ በዓለም ላይ ያሉ ምርጥ ብሔራዊ ቡድኖች የሚወዳደሩበት ነው፡፡ ስለኾነም ጨዋታውን የሚመሩ ምርጥ ዳኞችን ከዓለም ማዕዘናት መምረጥ ግድ ብሎናል” ነው ያሉት። የተመረጡት ዳኞችም በአውሮፓ ሀገራት እና በደቡብ አሜሪካ ትልልቅ ውድድሮችን በመምራት የታወቁ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ ጨዋታውን ለመምራት ከወዲሁ በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ከአውሮፓ ሀገራት ውጭ የተመረጡ አንድ ዳኛ ብቻ መኾናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ከ19ኙ የእግር ኳስ ዳኞች መካከል ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ጣልያን እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዳኞችን አስመርጠዋል፡፡
ከአውሮፓ ሀገራት ውጭ ከምትገኘው አርጀንቲና አንድ ዳኛ እንደተመረጡ ተጠቁሟል፡፡ 10 ዳኞች ደግሞ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የተመረጡ ናቸው ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበርን ጠቅሶ አስነብቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!