ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሜየር ሊግ ዛሬ ብራይተን በሜዳው ከማንቸስተር ሲቲ ተስተካካይ ጨዋታ ያደርጋል። በሊጉ 32 ጨዋታዎችን አድርጎ 73 ነጥብ በመያዝ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ነጥቡን 76 በማድረስ በሁለተኛነት እንዲቀመጥ ያስችለዋል። በመኾኑም ጨዋታው ለማንቸስተር ሲቲ ወሳኝ ነው ተብሏል።
አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ “በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባናል ብለዋል። ጋርዲዮላ አክለውም “ብራይተን ቀላል የሚባል ቡድን ባለመኾኑ ለሚጠብቀን ከባድ ፈተና ራሳችንን አዘጋጅተናል፤ እናሸንፋለንም” ሲሉ መናገራቸውን ዴይሊ ሜይል አስነብቧል። ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው 13 ጨዋታዎች ማንቸስተር በ11ዱ አሸንፏል።
በዛሬው ጨዋታ የማንቸስተር ሲቲን ቡድን ጁሊያን አልቫሬዝ የሚመራ ይኾናል። በአንጻሩ የቡድኑ ‘ሞተር’ ኤርሊንግ ሀላንድ በጉዳት ጨዋታው እንደሚያልፈው ተጠቁሟል። ብራይተን በሊጉ 32 ጨዋታዎችን አድርጎ በ44 ነጥብ እና በሁለት የግብ ግፍያ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አሠልጣኝ ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ በበኩላቸው ኤርሊንግ ሀላንድ አለመሰለፉ ለእኛ ጥሩ ዜና ነው። እሱ አንድ ተጫዋች ብቻ ስላልኾነ እድሉን ተጠቅመን ለማሸነፍ እንጫወታለን በማለት አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል። ቡድኑ ዜጎችን ማሸነፍ ከቻለም በ47 ነጥብ እና በአራት የግብ ክፍያ ዘጠነኛ ደረጃን ከያዘው ከቼልሲ በነጥብ እኩል ኾኖ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ ከ11ኛ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ የሚል ይኾናል።
ብራይተን በሊጉ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ካደረጋቸው 13 የቅርብ ጊዜያት ጨዋታዎች መካከል በ11ዱ እጁን ሰጥቷል። በኦፕታ ኮምፒዩተር ቅድመ ግምት መሰረት ማንቸስተር ሲቲ በ57 ነጥብ 4 በመቶ ያሸንፋል።
በትናንት የፕሪሜየር ጨዋታዎች በርንማውዝ ዎልቭስን 1ለ0፣ ክሪስታል ፓላስ ኒውካስትልን 2ለ0፣ ኤቨርተን ሊቨርፑልን 2ለ0 እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ሼፊልድ ዩናይትድን 4ለ2 ማሸነፋቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!