ባሕር ዳር: ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሌስተር ሲቲ በእግር ኳስ የመውደቅ እና መነሳት ምሳሌ የሚኾን ክለብ ነው። የቅርብ ጊዜ ታሪኩን ስንመለከት እ.አ.አ በ2008/2009 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን የቢቢሲ መረጃ ያሳያል። በ2015/16 የውድድር ዘመን ደግሞ የማይታመነውን ገድል በመፈጸም የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ባለቤት ኾነ። በ2021 የኤፍኤካፕ ዋንጫን በማንሳት ጥንካሬውን አሳይቷል።
እነዚህን ድሎች ያስመዘገበው ሌስተር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመንሸራተት ባለፈው የውደድር ዓመት ከፕሪምየር ሊጉ ለመውረድ ተገዷል። ታምረኛው ክለብ አሁን ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመለስ ጫፍ ደርሷል። ሻምፒን ሺፑን እየመራ ያለው ሌስተር ከሳውዝአፕተን ጋር የነበረበትን ወሳኝ ጨዋታ አምስት ለባዶ በኾነ ውጤት አሸንፏል። ይህን ተከትሎም ነጥቡ 94 ደርሷል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሊድስ ዩናይትድ በአራት ነጥብ ከፍ ማለትም ችሏል።
ይህም ‘ቀበሮዎቹ ‘ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ጫፍ እንዲደርሱ አግዟቸዋል። በቀጣይ ከፕሪስቶን እና ብላክበርን ከሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፍም ወደ ፕሪምየር ሊጉ በቀጥታ ያሳድጋቸዋል። በሻምፒዮን ሺፑ 90 ነጥቦችን የሠበሠበው ሊድስ ይናይትድ ሌስተርን ይከተላል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኢፒስዊች 89 ነጥብ በመያዝ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በውድድሩ መጨረሻ አንደኛ እና ሁለተኛ ኾነው የሚያጠናቅቁ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚያልፉ ይኾናል። ሦስተኛውን አላፊ ቡድን ለመለየት ደግሞ የተሻለ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የስካይ ቢት መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ: አስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!