ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወሳኝ የዋንጫ ፍክክር ውስጥ የሚገኘው አርሰናል በሜዳው ቼልሲን ይጋብዛል። መድፈኞቹ ከሳምንት በፊት በአስቶንቫላ ተሸንፈው ከሊጉ መሪነት ወርደው ነበር። ነገር ግን ከሽንፈታቸው ማግስት ዎልቭስን በማሸነፍቸው እና የሲቲ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አለማድረግን ተከትሎ አሁን ፕሪምየር ሊጉን እየመሩ ነው።
ቼልሲ የዘንድሮ የፕሪምየር ጉዞው በተጠበቀው ልክ አይደለም። አሠልጣኙ ፖችቲኖም በክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሞ እያስተናገዱ ነው። ይሄም ኾኖ ከተወሰኑ ጊዚያት ወዲህ መሻሻሎች አሳይቷል።
እንደቢቢሲ ዘገባም ሰማያውዮቹ በፕሪምየር ሊጉ በስምንት ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገዱም። አራቱን ሲያሸንፉ፣ ቀሪ አራቱን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በተለይ ግብ በማስቆጠር በኩል ክለቡ ትልቅ መሻሻል አሳይቷል። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በትንሹ በጨዋታ ሁለት ግብ በተጋጣሚዎቹ ላይ ማስቆጠሩ ለመሻሻሉ ማሳያ ነው።
በባለሜዳው አርሰናል በኩል የረዥም ጊዜ ጉዳት ካለበት ጁሊያን ቲምበር ወጭ ጉዳት የለም። በቼልሲ በኩል ግን የክለቡ ቁልፍ ተጫዋች ኮል ፓልመር በጨዋታው መሰለፉ ጥያቄ ውስጥ ነው። ተጫዋቹ በማንቼስተር ሲቲ ከተሸነፉበት የኤፍኤካፕ ጨዋታ በኋላ በህመም ምክኒያት ልምምድ አለመሥራቱን ቢቢሲ አስነብቧል። ተከላካዮቹ ችልዌል እና ሚሎ ጉስቶም መሰለፍ አለመሰለፋቸው የዘገየ ውሳኔ ይፈልጋል ነው የተባለው።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!