ኢንተር ሚላን 20ኛ የሴሪኤ ዋንጫውን አነሳ።

0
227

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢንተር ሚላን የ2023/24 የጣሊያን ሴሪኤ ዋንጫ ማሸነፉን አረጋግጧል፡፡ በጣሊያን ሲሪኤ 33ኛ ሳምንት የምንጊዜም ተቀናቃኙን ኤሲ ሚላንን የገጠመው ኢንተር ሚላን ጨዋታውን በማሸነፍ “የስኩዴቶውን” ክብር ለ20ኛ ጊዜ ማሸነፉን አረጋግጧል፡፡
የኢንተር ሚላንን የማሸነፊያ ግቦች ፍራንሲስኮ አቼርብ እና ማርከስ ቱራም አስቆጥረዋል፡፡ ሦስት የቀይ ካርዶች በተመዘዙበት በዚህ ጨዋታ የዋንጫ ባለቤት የሚያደርገውን ድል አስመዝግቧል፡፡

ኢንተር ሚላን “የስኩዴቶውን ክብር ያሳካው ሊጉ አምስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከተከታዩ ኤሲሚላን በ17 ነጥቦች በመራቅ ነው፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ ኢንተር በሚላን ደርቢ ድል አድርጎ ዋንጫውን ማንሳቱን ሲያረጋግጥ በ116 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

የኢንተር ሚላኑ አምበል ላውታሮ ማርቲኔዝ ጠንከረን ስለሠራን ደስታው ይገባናል ብሏል፡፡ ኢንተር ሚላን 20ኛውን “የስኩዲቶ” ክብር ማሳካቱን ተከትሎ በጣሊያን ሴሪኤ በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ሁለተኛው ቡድን ኾኗል፡፡ ኢንተር በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት የሚበለጠው በጁቬንቱስ ብቻ ነው፡፡ የምንጊዜም ተቀናቃኙ ኤሲሚላን ደግሞ 19 ጊዜ በማንሳት ከኢንተር አንሶ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያመላክተው ኢንተር እ.አ.አ ከ2010 ወዲህ ድል ሲያደርግ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በ2021 በአንቶኒዮ ኮንቴ ስር “የስኩዲቶውን” ክብር ማሳካቱ ይታወሳል፡፡ ኢንተር ሚላን ያለፉት ስድስት የደርቢ ጨዋታ በማሸነፍ የምንጊዜም ተቀናቃኙ ኤሲሚላን ከ1911 እስከ 1913 እና ከ1946 እስከ 1948 ካሳካው ክብረ ወሰን ጋር መስተካከል ችሏል፡፡

ኢንተር ሚላን አምስት ጨዋታዎች እየቀሩት 86 ነጥቦች እና 61 የግብ ክፍያዎች አሉት፡፡ ተከታዩ ኤሲ ሚላን ደግሞ 69 ነጥቦች እና 25 የግብ ክፍያዎችን ይዟል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here