ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተስፋዬ አያሌው በ1970ዎቹ መጀመሪያ በቡድን ስፖርት በተለይም በእግር ኳስ የተማሪዎች ምርጥ ቡድን ይጫወት ነበር። በ70ዎቹ አጋማሽ ደግሞ ለደብረታቦር አውራጃ ምርጥ እግር ኳስ ቡድን ተጫውቷል። በዚያ ዘመን ስፖርት በሕዝባዊ ቅቡልነትም ኾነ በሥነ ምግባር ዓላማውን ያልሳተ እንደነበር ያስታውሳል።
በእነ ተስፋዬ ዘመን ወጣቱ በየቀበሌው ለስፖርት ይደራጃል፤ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በደብረታቦር ከተማ አጅባር ሜዳ በመገናኘት የጋራ ስፖርት እና ሩጫ ይዘወተራል። ተስፋዬም ተሳታፊም፣ አሠልጣኝም ኾኖ ሠርቷል። የእግር ኳስ ስፖርት ቡድን በየቀበሌው ሲቋቋም ቀበሌዎች የማሊያ እና የጫማ ድጋፍ፤ ሕዝቡ ደግሞ ውድድሮችን በመመልከት የሞራል ድጋፍ ያደርጋል። አሠልጣኝ ተመድቦም ከሠፈር ጀምሮ ሥልጠና ይሰጣል።
በወቅቱ ስፖርትን ለወዳጅነት፣ ለጤንነት በሚል መርሕ ይዘወተር እና ውድድር ይደረግ እንደነበር ነው ተስፋዬ የሚናገረው። የሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ ውድድሮች በቀበሌ እና በትምህርት ቤቶች ይደረጋሉ። እግር ኳስ በአውራጃ እና በክፍለ ሀገር ውድድር ከሚደረግባቸው መካከል ትኩረት ሳቢ እንደነበርም ተስፋዬ ያስታውሳል። ”ሁለገብ ኾነን በእያንዳንዱ ስፖርት ላይ እንሳተፍ ነበር” ያለው ተስፋዬ አንድ ወጣት በሩጫ፣ መረብ እና እግር ኳስ ላይ በንቃት መሳተፉ የተለመደ እንደነበር ይናገራል።
”እኔ በይበልጥ እግር ኳሱ ላይ ነበር የማተኩረው፤ በ7 እና 11 ቁጥር በአጥቂ ቦታ ነበር የምጫወተው” ይላል። ተስፋዬ በደብረታቦር አውራጃ ለተማሪዎች ምርጥ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል፤ ለዋንጫም በቅቷል። የዚያ ዘመን ወጣት ብቻ ሳይኾን ጎልማሳውም፣ ሽማግሌውም ለስፖርት ፍቅር እና አክብሮት ስላለው ይከታተል እና ይደግፍ እንደነበር ያስታውሳል። ”በየሳምንቱ እሑድ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ሲካሄዱ ማኅበረሰቡም በአጅባር ሜዳ በመገኘት በውድድሩ ይዝናናል፤ ስፖርተኞችን ያበረታታ ነበር” ሲል ያስታውሳል።
ተጫዋቾች እንደየ ችሎታቸው እና አጋጣሚዎቹ በቅጽል ስም ይጠሩ እንደነበር የገለጸው ተስፋዬ ”ቸንቶ” የሚል ቅጽል ስም እንዳለው እና አሁንም እንደሚጠራበት ገልጿል። ”ተስፋዬ ቸንቶ፤ ይመታል ለክቶ” ይባልለትም ነበር። እነ ሙሉጌታ ዘንዶ፣ ሐይሌ ጅቦ፣ ፈረደ አረጋዊ፣ ጋሻው ጊላ፣ ፋሼታ፣ ጓድሽ ጓዳ፣ በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩ ስፖርተኞችንም ይጠቅሳል። ስሙ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴያቸው ጋር ስለሚገናኝ ይወዱታልም።
ስፖርት እንደዛሬው የገቢ ምንጭ እና መተዳደሪያ ባልነበረበት ጊዜ እነተስፋዬ የሚጫወቱት ለጤና፣ ለጥንካሬ፣ ለመዝናኛ እና የሚወክሉትን ማኅበረሰብ ለማስደሰት እና ሀገርን ለማስጠራት ነበር። ስፖርታዊ ሥነ ምግባሩም ከፍተኛ እና ጨዋነት የተሞላበት እንደነበር ይገልጻል። ”ዛሬ ላይ ስፖርት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው የሚለው ተስፋየ ወጣቱ ግን አልተጠቀመበትም” ባይ ነው። እንዲያውም ለስፖርት ባላቸው ፍቅር የቀድሞዎቹ አሁንም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደኾኑ ተናግሯል። ተስፋዬ አሁንም ንቁ፣ እና ጤነኛ ኾኖ ይታያል። ይህ ደግሞ የስፖርት ውጤት መኾኑን ይመሰክራል። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የቀድሞ የአውራጃው ተጫዋቾች ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር መደጋገፍ እና መተባበራቸውን ቀጥለዋል። ሲመቻቸው እየተገናኙ ትዝታቸውን እያስታወሱ ይዝናናሉ፤ ይደጋገፋሉ፤ የወዳጅነት ስፖርታዊ ውድድርም ያደርጋሉ። ”በዚህም ለአሁኑ ትውልድ አርዓያ መኾናችንን ቀጥለናል” ብሏል ተስፋዬ። የአሁኑ ወጣት ስፖርትን ለጤና፣ ሀገርን እና ሕዝብን ወክሎ ለማኩራት፣ ለፍቅር እና ለአንድነት ሊጠቀምበት እንደሚገባ አሳስቧል።
አሁን ላይ ሁለገብ የስፖርት ማኅበረሰብን ለመፍጠር ምን እየተሠራ እንደኾነ በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሸዋስ ጌታሁንን አስተያየት ጠይቀናል። ስፖርት ከመሠረቱ ለመጀመር ዕድሜው ከአምስት እስከ 65 ዓመት ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ፣ የተለየ ችሎታ ያላቸውን የመምረጥ፣ በፕሮጀክት የማስገባት እና ምርጥ ፕሮፌሽናሎች ሀገርን እንዲወክሉ የማድረግ አሠራር መኖሩን ጠቅሰዋል።
በስፖርት ለሁሉም ፕሮግራም ኅብረተሰቡ ያለ እድሜ ገደብ በስፖርት እንዲሳተፍ ከሚደረግበት አደረጃጀት ውስጥ አንዱ የጤና ቡድን መኾኑን አቶ የሸዋስ ጠቅሰዋል። የመሥሪያ ቤቶች የስፖርት ውድድርም ሌላኛው የማስ ስፖርትን የማስፋፊያ መንገዶች ኾነው እየተሠራባቸው ነው ብለዋል። ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ ‘ስፖርት ለሁሉም’ ሳምንት ከመጋቢት 23/2016 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28/2016 ዓ.ም በተለያዩ ስፖርታዊ ኹነቶች መከበሩን የገለጹት ኀላፊው ዩኒቨርሲቲዎችም ለማስ ስፖርት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የስፖርት ተዋረዳዊ ተቋማት የማስ ስፖርትን ለማጠናከር የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው ውድድር እና ነጥብ የሚያስገኙ ስፖርቶች ላይ የማተኮር ዝንባሌ ይታያል ብለዋል። ካለፈው ትውልድም ለመማማር ያለው ጥረት ውሱን መኾኑን ነው አቶ የሸዋስ የተናገሩት።
አቶ የሸዋስ ማኅበረሰቡ ለራሱ ጤንነት ሲል ስፖርትን ማዘውተር እና ባሕል ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። የኅብረተሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች እና የሚዲያ ተቋማት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሳይኾን ጤናውን በስፖርት የሚጠብቅ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!