በ22ተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማን ከአዳማ ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ ትኩረት አግኝቷል።

0
210

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሪምየር ሊጉ በ22ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ትናንት ሁለት ጨዋታዎችን አስተናግዷል። የተሻለ መነቃቃት ላይ የነበረው ባሕር ዳር ከተማ በተከታታይ ነጥብ የጣለበትም ኾኗል። ሳምንት በጠባቂው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሦስት ነጥብ ለመውሰድ ተቃርበው የነበሩት ሞገዶቹ በመጨረሻው ደቂቃ ግብ አስተናግደው ነጥብ መጋራታቸው ይታወሳል።

ትናንት ከሀድያ ጋር ያደረጉትን ጨዋታም አቻ አጠናቀዋል። ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ እየተጠጉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በተከታታይ ነጥብ መጣላቸው ወደዋንጫ ፉክክሩ ይበልጥ እንዳይቀርቡ አድርጓቸዋል። ትናንት በተካሄደ ሌላ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ወልቂጤን 3 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲኾን ቀን 10 ሰዓት ሀምበሪቾ ከሀዋሳ፣ ምሽት 1 ሰዓት ደግሞ ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ። በተለይ በፋሲል እና አዳማ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚታይበት ይጠበቃል። አጼዎቹ በደረጃ ሰንጠረዡ በ32 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ተጋጣሚያቸው አዳማ ደግሞ በአንድ ነጥብ ተሽሎ ስድስተኛ ላይ ተቀምጧል።

በፋሲል በኩል የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙ ተጫዋቾች በተጨማሪ ናትናኤል ገብረ ጊዮርጊስ በጉዳት እንደማይሰለፍ የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያሳያል። ሀቢብ መሐመድ ደግሞ በቅጣት ምክኒያት ጨዋታው ያልፈዋል። በአዳማዎች በኩል ቦና አሊ ለጨዋታው ብቁ አይደለም። ጨዋታው ምሽት እንድ ሰዓት ይጀምራል።

ቀን 10 ሰዓት ወራጅ ውስጥ የሚገኘው ሀምበሪቾ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታል። ሀምበሪቾ ስምንት ነጥብ ይዞ በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ነገርግን ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ የሚመሰገን እንቅስቃሴ አሳይቶ ነጥብ ተጋርቷል። ለዛሬው ጨዋታም መነቃቂያ ይኾነዋል እየተባለ ነው።

ሀዋሳ ከተማ የዘንድሮ ጥንካሬው የአጥቂው አሊ ሱሌማን ድንቅ ብቃት ላይ መገኘት ነው። ከዚህ ውጭ ቡድኑ በሚታወቅበት ተፎካካሪነት ላይ አይገኝም። የዛሬውን ጨዋታ የሚያደርገውም ከተከታታይ ሽንፈት መልስ ነው። ቡድኑ በ26 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይም ይገኛል።

ዘጋቢ: አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here