በፓሪስ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ ዘርፍ የወርቅ ሜዳሊያ ለሚያመጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ሊሰጥ ነው።

0
231

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2024ቱ ኦሎምፒክ ለአትሌቶች ገንዘብ እንደሚሸልም አስታውቋል። የዓለም የብስክሌት ኅብረት በበኩሉ የሽልማት ሃሳቡን ተቃውሞታል፡፡ በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከነሐሴ 1 እስከ 11/ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲከናወን መርሐ ግብር ተይዞለታል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ለሚያመጡ አትሌቶች 50ሺህ ዶላር ለመስጠት መወሰኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ፌዴሬሽኑም በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የሽልማት ገንዘብ የሚያቀርብ የመጀመሪያው ፌዴሬሽን ይኾናል ነው የተባለው።

ዓለም አቀፉ የብስክሌት ኅብረት ደግሞ አትሌቶችን ብቻ ለይቶ ለመሸለም የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡ የኦሎምፒክን መንፈስን የሚጻረር ነው በማለት ተቃውሞታል፡፡ የብስክሌት ኅብረቱ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ላፕፓርት “ ሽልማቱ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ከውድድር የሚያስቀር በመኾኑ እንቃወመዋለን፤ በቀረበው ሃሳብ ላይ የብስክሌት ኅብረቱ አይተባበርም” ብለዋል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ሎርድ ኮ “ሽልማቱ አትሌቶች በስፖርቱ ዓለም ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ እና ለውድድሩ ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላል፤ ሌሎች ፌዴሬሽኖችም ስፖርተኞቻቸውን ለማትጋት በተናጠል ሽልማት ቢያዘጋጁ ስፖርቱን ያሳድገዋል እንጅ አይጎዳውም “በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here