ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 21ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 17ኛው የባሕል ፌስቲቫል ከሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 20/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ከክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ልዑካን የሚሳተፉ ሲሆን ተወዳዳሪዎች በ11 የስፖርት ዓይነቶች ይፎካከራሉ።
ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተሳታፊ መኾናቸውም ተገልጿል። የውድድሩን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር በጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ለውድድሩ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ሕይወት መሀመድ የውድድር ስፍራዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል። የማንነት መገለጫ የኾኑት የባሕል ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲኖራቸው ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በርካታ ዲፕሎማቶች በሚገኙባት አዲስ አበባ ውድድሩ መካሄዱ አጋዥ እንደሚኾንም ወይዘሮ ሕይወት ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ በላይ ደጀን አዲስ አበባ የሚመጡ ልዑካንን በአግባቡ ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ውድድሩ ከጅማሬው እስከ ፋፃሜው የተሳካ እንዲኾንም የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንመ ጠቁመዋል፡፡
በባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የባሕል ስፖርቶች ማኅበረሰባዊ አንድነትን ለማጠናከር እና የባሕል ትስስርን ለማጎልበት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸው ውድድሩ እነዚህን እሴቶች በጠበቀ መልኩ መካሄድ እንዳለበት ተናግረዋል።
ለዘመናዊ ስፖርቶች መነሻ የኾኑት የባሕል ስፖርቶችን ለማልማት እና ለማሳደግ እንደ መንግሥት ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!