ውድድሩ በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የግንዛቤ ማስጨበጫ አንዱ አካል ነው ተብሏል። “ኢትዮጵያ ታምርት ” በሚል መሪ መልዕክት የተዘጋጀውን የሩጫ ውድድር አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ናቸው፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ውድድሩ ሲዘጋጅ አምራች ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባሕልን ግንዛቤ መፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የስፖርት ትጥቆችን ማስተዋወቅ፣ የገቢያ ትስስርን መፍጠር እና የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብን ከስፖርት ጋር ማስተሳሰር ሌላኛው ምክንያት እንደኾነ ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።
በውድድሩ ታዋቂ አትሌቶች፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ሠራተኞች እና ከኢምባሲዎች የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ከተሳታፊዎቹ መካከልም 9 ሺህ የሚኾኑት ከአምራች ኢንዱስትሪው የተውጣጡ ናቸው። በታዋቂ አትሌቶች ዘርፍ ደግሞ ከ22 ክለቦች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ አትሌቶች ተሳታፊ መኾናቸው ታውቋል።
ለውድድሩ ቅድመ ዝግጅቶች መሠራታቸውን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ውድድር ለሚያሸንፉ አትሌቶች የሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ውድድሩ መነሻውን እና መዳረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ሚያዝያ 13/2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!