ባሕር ዳር: ሚያዚያ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎችን እያከናወነ ነው። ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች መከናወናቸው ይታወሳል። የመልስ ጨዋታዎች ደግሞ ዛሬ እና ነገ ይከናወናሉ። በዛሬው መርሐግብር ባርሴሎና ከፒኤስጅ እና ቦሩሲያዶርትሙንድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ይጫወታሉ።
የመጀመሪያው የባርሴሎና እና ፒኤስጅ ጨዋታ ባርሴሎናን አሸናፊ አድርጓል። ፓሪስ ላይ የተካሄደውን ጨዋታ 3 ለ 2 የረታው የዣቪው ቡድን የዛሬውን ጨዋታ በሜዳው የሚከናወን በመኾኑ የተሻለ እድል አለው። የባርሴሎናው አሠልጣኝ ዣቪ ሄርናዴዝ ግን “የመጀመሪያውን ጨዋታ አሸንፈናል ብለን አንዘናጋም ዛሬም ለማሸነፍ እንጫወታለን “ብሏል።
በተመሳሳይ የቀድሞው የባርሴሎና የአሁኑ የፒኤስጅ አሠልጣኝ ሊዊስ ሄነሪኬ ውጤቱን ቀልብሰን ግማሽ ፍጻሜ እንደርሳለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። “ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥሩ አንድነት ያለው የቡድን ስብስብ አለን” ብለዋል። ነገር ግን ታሪክ ስለፒኤስጅ ጥሩ ነገር አይናገርም። ክለቡ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በመጀመሪያ ዙር በተሸነፈባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ውጤት ቀልብሶ ወደቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለም።
ሁለቱ ክለቦች 14 ጊዜ መገናኘታቸውን ታሪክ ያወሳል። ስድስቱን ባርሴሎና፣ አራቱን ፒኤስጅ ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ አቻ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው። በሌላ የዛሬ ምሽት መርሐግብር ቦሩሲያዶርትሙንድ በሜዳው አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናጋዳል።የመጀመሪያውን ጨዋታ 2 ለ 1 ረቷል። ነገር ግን የጀርመኑ ክለብ ከሜዳው ውጭ ያስቆጠራት ግብ ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ ተስፍ ኾናዋለች። በተጨማሪም በድጋፍ አሰጣጥ ምሳሌ የሚኾኑት የክለቡ ደጋፊዎች ለቢጫ ለባሾቹ ሌላ ጥንካሬ ናቸው።
ጨዋታዎቹ ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምሩ ይኾናል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!