ባሕር ዳር: ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጀርመን እግር ኳስ ረዥም እድሜ ካስቆጠሩ ክለቦች መካከል ባየር ሊቨርኩሰን ተጠቃሽ ነው። ነገር ግን ክለቡ በእነዚህ ዓመታት ከዋንጫ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም። አንደጎል መረጃ በ120 ዓመታት ረዥም መንገዱ በቦንደስሊጋው በአምስት አጋጣሚ ለዋንጫ የቀረበ ጉዞ አድርጎ ነበር። ነገር ግን ሊጉን በመራባቸው እና የድል ራቡን አስታገሰ ሲባል ወደ ኋላ የሸሸባቸው አጋጣሚዎች ኾነው አልፈዋል። ይሄ የዋንጫ አይናፋርነቱን ከእድሜ ጠገብነቱ ጋር ተዳምሮ በጀርመን ምድር “ኔቨርኩሰን” የሚል የስላቅ ስም እስከማግኘት ደርሷል፤ ሊቨርኩሰን ዋንጫ መቼም አይበላም የሚለውን ሃሳብ ለመግለጽ የተሰጠም ነው።
አሁን ታሪክ ተቀይሯል፤ በዣቪ አሎንሶ የሚመራው ቡድን የቦንደስ ሊጋውን ዋንጫ አንስቷል። ከ18 ወራት በፊት በሊጉ እንኳ የመቆየት አደጋ የነበረበት ቡድን፤ ስፔናዊ አሠልጣኝ መላክ ኾኖለት ዛሬ ከባየርሙኒክ በላይ ኾኖ የማይታመነውን አድርጓል። ከዚህ በኋላ ሊቨርኩሰን ኔቨርኩሰን እየተባለ መሳለቂያ አይኾንም። አሠልጣኙ አሎንሶ ትናንት ወርደርብሬመንን አሸንፈው ዋንጫውን ማንሳታቸውን ሲያረጋግጡ ከዚህ በኋላ ኔቨር የሚባል ነገር የለም ማለታቸውም ለዚህ ነው።
ባየርሊቨርኩሰን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሽንፈት ያልገጠመው ብቸኛው የአውሮፓ ቡድን ነው። በ43 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ግስጋሴ ላይ ይገኛል። በጀርመን ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ ነው። በዩሮፓ ሊግም ለዋንጫ የተሻለ ከተገመቱት ክለቦች መካከል ኾኗል። ለሊቨርኩሰን አሁን እዚህ ደረጃ ላይ መገኘት እንደ ቡድን የተሠራው ሥራ ምሳሌ ቢኾንም ቀዳሚው ግን አሠልጣኙ አሎንሶ ነው። በእግር ኳስ ከታዩ ምርጥ የመሐል ተጫዋቾች አንዱ እንደነበር የሚመሰከርለት አሎንሶ አሁን በአሠልጣኝነትም አንቱ ሊባል ስኬትን አንድ ብሏል።
ፔፕ ጋርዲዮላ በባየር ሙኒክ አሠልጣኝ እያሉ አሎንሶ ተጫዋቻቸው ነበር። አሎንሶ ጫማውን ሲሰቅል “በእግር ኳስ ካየኋቸው ምርጥ አማካዮች አንዱ ነው፤ በእርግጠኝነት አሎንሶ ምርጥ አሠልጣኝ ኾኖ ወደ እግር ኳሱ ይመለሳል” የሚል ሃሳብ ሰጥተው ነበር። አሎንሶ በጋርዲዮላ ሚዛን ተገኝቷል።
ከዓመት በፊት ለመውረድ ጫፍ የደረሰውን ቡድን አሁን አስፈሪ ቡድን አድርጓል። 3-4-2-1 የጨዋታ አቀራርብን የሚመርጠው አሎንሶ የማያቋርጥ ማጥቃትን የሚተገብር ቡድን ሠርቷል። ስፔናዊ አሠልጣኝ ክለቡን ከመረከቡ በፊት በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦችን ያስተናግድ ነበር። ዘንድሮ በቦንደስ ሊጋው 19 ግቦች ብቻ ተቆጥረውበታል። ይህም ከባየርሙኒክ በ17 ግቦች ያነሰ መኾኑን ልብ ይሏል።
አሎንሶ ተጫዋቾችን የሚጠቀምበት መንገድም እያስወደሰው ነው። በየክለባቸው ምርጥ ጊዜያቸው አልፏል የተባሉ ተጫዋቾችን እንደ አዲስ ስሎ የቡድኑ መሠረት አድርጓቸዋል። ከአርሰናል የወጣው ዣካ ለዚህ ትልቁ ማሳያ ነው። ዣካ በሊቨርኩሰን የቡድኑ የመሐል ክፍሉ ልብ ነው። አልፎ አልፎ ከርቀት የሚያስቆጥራቸው ግቦችም ለቡድኑ ስኬት ድርሻ አላቸው። ከደካማው ቤልጀም ሊግ ናይጀሪያዊ አጥቂ ቪክቶር ቦኒፌስ አምጥቶ የቡድኑ ቁልፍ አጥቂ ማድረጉም ሌላ የሚያሥመሠግነው ነው።
በጀርመን እግር ኳስ ባየርሙኒክ የውጤታማነት መለኪያ ቁና ነው። ለባለፉት 11 ተከታታይ ጊዜያት ቦንደስሊጋውን አሸንፏል። ዘንድሮ ግን በሊቨርኩሰን ዋንጫውን ከመነጠቁ በፊት አሁን በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 16 መኾኑ ሲታይ የሊቨርኩሰንን የጥንካሬ ደረጃ ያሳያል።
ለዘመናት መዘባበቻ የነበረው ባየርሊቨርኩሰን ቀሪ ጊዜው ብሩህ ይመስላል። በጀርመን ዋንጫ ለመውሰድ የተሻለ እድል አለው። አምና ግማሽ ፍጻሜ ድረስ በተጓዘበት ዩሮፓ ሊግም የእስካሁን መንገዱ የሰመረ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ በትልልቅ ክለቦች ሲታደን የነበረው አሠልጣኙ አሎንሶ በክለቡ ይቆያል።
በየርገን ክሎፕ” የአዲሱ ትውልድ ጨዋታ ቀያሪ ታክቲሻን” ተብሎ የተሞገሰው አሎንሶ በሊቨርፑል እና ባየርሙኒክ በጥብቅ ቢፈለግም ከክለቡ ጋር መቀጠልን መርጧል። ይህም የቡድኑ ባለቤቶችን እና ደጋፊዎችን ደስታ ድርብ አድርጓል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!