በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል።

0
290

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የሚደረገው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ምሽት አንድ ሰዓት ሲል ይጀምራል። ባለፈው ዓመት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እስከ መጨረሻው የተፋለሙት እንዚህ ቡድኖች ዘንድሮ ንግድ ባንክ እና መቻልን የመሳሰሉ ቡድኖች በጥንካሬ ከፊታቸው ቆመዋል።

የጣና ሞገዶቹ በመጀመሪያው የውድድር አጋማሽ ያሳዩት አቋም ብዙ ያስተቻቸው ነበር። ነገር ግን አሁን የተለየ ጥንካሬ ላይ ይገኛሉ። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ሦስት ነጥብ ሲያስመዘግቡ በአንዱ ብቻ ነጥብ ተጋርተዋል። ለቡድኑ ውጤት ማማር የቡድኑ የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ የሚደነቅ ነው። በያሬድ ባየ የሚመራው የሞገዶቹ የኋላ ክፍል ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግብ አላስተናገደም።

በሌላ በኩል የፈረሰኞቹ ወቅታዊ ብቃት አስተማማኝ አይመስልም። በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ የሚገኙት ፈረሰኞቹ በተከታታይ የጣሏቸው ነጥቦች ከመሪዎች ያላቸው ነጥብ እንዲሰፋ አድርጓል። ጨዋታው ምሽት አንድ ሰዓት የሚጀምር ሲኾን ባሕር ዳር ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት ነጻ የኾነ ሙሉ የቡድን ስብስቡን ይጠቀማል። ጊዮርጊሶች ግን የመሀል ተጫዋቹ በረከት ወልዴን በቅጣት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ዘጠኝ ጊዜ የተገናኙ ሲኾን ሦስቱን የጣና ሞገዶቹ፣ ሁለቱን ፈረሰኞቹ አሸናፊ ኾነዋል። በቀሪዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል። በእለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሀምበሪቾን ይገጥማል። በጉዳት ቡድናቸው የሳሳው አጼዎቹ የባለፈው ሳምንት የድሬዳዋ ሽንፈትን ጨምሮ ከድል እርቀዋል። ቡድኑ በተለይ በመከላከል የሚታወቅበትን ጥንካሬ ባለፉት ጨዋታዎች አጥቷል። በቅርብ ሦስት ጨዋታዎችም አምስት ግቦችን አስተናግዷል።

ሀምበሪቾ በሊጉ ለመቆየት ነገሮችን ማቅለል አልቻለም። በቅርብ ስምንት ጨዋታዎች በሰባቱ መሸነፉ የሊጉ ቆይታው ላይ ቀሪ ሥራው የከበደ እንዲኾን ያደርግበታል። ፋሲል ከነማ አማኑኤልን በረዥም ጉዳት ከማጣቱ ባለፈ ጋቶችን በቅጣት አያሰልፍም። ተከላካዮቹ አምሳሉ ጥላሁን እና ዓለም ብርሀን ይግዛውም ለጨዋታ ብቁ መኾናቸው እርግጥ አይደለም። እንደ ሶከር ኢትዮጵያ መልካሙ ነገር የአጥቂው ጌታነህ ከበደ በሙሉ ጤንነት መገኘት ነው።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here